የስታቲስቲክሱና የገበያው መለያየት እንቆቅልሽ – ጌታቸው አስፋው (የብሔራዊ ኢኮኖሚ ዕቅድ ባለሙያ)

ጌታቸው አስፋው / Black Lion
(የብሔራዊ ኢኮኖሚ ዕቅድ ባለሙያ)
Related image

በገበያ የቀረበው የገንዘብ መጠን በገበያ ዋጋ ካልተለካው ምርት ጋር ሊመጣጠን ባለመቻሉ በዋጋ ግሽበት የሰደድ እሳት ተቃጠልን፣ በሸቀጥ ዋጋ ጭቅጭቅና ንትርክ ውስጥ ገባን፣ ዋጋዎች በቀናትና በሳምንታት ተለዋወጡብን፡፡ ገቢ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ቢሆንም የገቢ ዕድገት ከምርታማነት ዕድገት በላይ ስለሆነ ገንዘቡ ዋጋ አጣ፡፡ ግልጽ ሥራ አጥነት በስውር ሥራ አጥነት ተተክቶ ምርታማነትን ቀነሰ፡፡ በጥቃቅን የተደራጁት ወጣቶች በሙሉ አቅማቸው ሳይሰሩ በነርሱ ላይ ሌሎች ማደራጀት የቀድሞዎቹንም አዲሶቹንም በሙሉ አቅማቸው ሠርተው ምርታማ እንዳይሆኑ አደረጋቸው፡፡

ሥራ ፈጠራ በብሎኬት ምርት፣ መስኮትና በር መግጠም፣ አልባሳት፣ ቦርሳና ቀበቶን የመሳሰሉ የግል መጠቀሚያዎችን ማምረት ጀምሮ አሁን ወደ ጀበና ቡና፣ ቦርዴ (ሻሜታ) ጠመቃ፣ የዐረብ ሱቅ፣ በቆርቆሮ ግድግዳ ደሳሳ ጎጆ የሆቴል ኪዎስክ ወርዷል ከዚህ በታች ወዴት እንደሚወርድ አይታወቅም፡፡ በየመንገድ ዳሩ ጠላ ጠምቆ መሸጥ ይሆናል፡፡ አምርቶ ገንዘብ ማግኘት ካልተቻለ አጭበርብሮም ቀምቶም ሰርቆም የሰው አካልን ደልሎም ገንዘብ ለማግኘት ይሞከራል፡፡ በውድድር ሳይሆን በሽሚያ ገንዘብ ለማግኘት ለመክበር መስገብገብ መሻማት መሻሻጥ መታወቂያችን ሆኗል፡፡ በሦስት ሺሕ ብር ሥራ ጀምሮ በዓመቱ ሦስት ሚልዮን ብር ካፒታል ማስመዝገብ፣ መቶ ሺሕ ብር ለደላላ ከፍሎ ወደሞት ለመሄድ መደራደር፣ ለደቂቃዎች መዝናኛ በሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ ማውጣት፣ ቅጥ ላጣ የውጭ አገር ጉዞ የቅንጦት ወጪ ማድረግ፣ ጥሬ ገንዘብ ከጓሮ የሚሸመጠጥ ቅጠል አስመስሏል፡፡ በየቴሌቪዥኑ መዝናኛ ፕሮግራም አቅራቢዎች ለእንግዶቻቸው የሃያ ሺሕ ብር ሐምሳ ሺሕ ብር የቀን ውሎ ጉርሻ ሲሰጡ ታይቷል፡፡ በ1960ዎቹ ቦሌ አስፋልት ዳር የነበረ ዘመናዊ ቪላ ቤት በአምስት ሺሕ ብር ይሸጥ እንደነበር የሚያውቅ ሰው ይኽን ሁሉ ጉድ ሲያይ ምን ይል ይሆን?

አምና በመቶ ብር መነሻ ካፒታል የከተማ ሥራ ጀምሬ ዘንድሮ ሦስት ሚልዮን ብር ካፒታል አለኝ፣ በግማሽ ሔክታር መሬት የግብርና ሥራ ዐሥር ሚልዮን ብር ካፒታል አለኝ፣ የሬድዮና የቴሌቪዥን ፕሮፓጋንዳ የወጣቱን ሥነ ልቦና ሰለበ፤ የሥራ ባህል ጠፋ፤ ገንዘብ ተሠርቶ የሚገኝ ሳይሆን ከሜዳ የሚታፈስ፣ ጓሮ ከበቀለ ዛፍ የሚሸመጠጥ መሰለ፤ መቶ ሺሕ በትኖ ሚልዮን ለማፈስ የተሰናዳ ትውልድ ተፈጠረ፤ ከሠርቶ በሌው አውርቶ በሌውና ዘሎ በሌው በዛ፣ የዩኒቨርሲቲ ትምህርትን አቋርጦ ጊታር ማንሳት ተለመደ፡፡

ግማሽ ያህሉን ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት በያዘው የአገልግሎት ምርት መሰማራት የሕዝቡን ገቢ ከምርታማነቱ በላይ በፍጥነት አሳደገ፣ ሎሚና እምቧይ ተቀላቅለው እየተቆጠሩ የአገር ውስጥ ምርት አብጦ ያደገ መሰለ፡፡ በአንዳንድ ሥራዎች ምርታማነት ሊጨምር ቢችልም በአገር ደረጃ ግን ምርታማነት ከመጨመር ይልቅ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ የተናጠል ምርታማነት የአገር ምርታማነት ሊሆን አልቻለም፡፡

በጤናውና በትምህርቱ ዘርፍ የሕዝቡን ምርታማነት ሊጨምሩ የሚችሉ ለውጦችና መሻሻያዎች ቢታዩም ሰውን ማልማት ባለዲግሪ መቁጠር መስሎን ቁጥር አምላኪዎች ሆነናል፣ በዚህም ላይ የምናፈራቸው ወጣቶች ፌርማታ ለባዕድ አገር ሎሌነት ሥራ መሆኑ ከቀጠለ አገራዊ ምርታማነት ሊያድግ አይችልም፡፡ በመሠረተልማት እና በሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶች ባለፉት ዓመታት የተሠሩት ስራዎች የህዝቡ የተጠቃሚነት ደረጃ እንደ የሀብት መደቡ፣ የሚኖርበት አካባቢ፣ የዕድሜው ክልል፣ ቢለያይም በጥቅሉ ለሁሉም ሰው ለኢኮኖሚ ዕድገትም ለልማትም ስለሚጠቅም መልካም ነው፡፡ በዚህ ምንም ተቃውሞና ትችት የለኝም፡፡

ሆኖም ለግለሰብ ሊሸጥ የሚችልና በግለሰብ ሊለማና የገበያ ዋጋ ሊኖረውም ይገባ የነበረን የገበያ ሸቀጥ የጋራ ልማት ሥራ አድርጎ በመንግሥት እጅ አፍኖ ይዞ የገበያ ዋጋ እንዳይኖረው ማድረግ፣ ምርቱን ትክክለኛ ዋጋ እንዳሳጣው ሳልገልጽ ግን አላልፍም፡፡

የጋራ በሆነ መሬት ላይ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና እንክብካቤ መሥራት የሚቻለው በጋራ ብቻ ነው፡፡ የጋራ የሆነም የግል አይደለም፤ የግል ያልሆነም ገበያ አይወጣም፤ ገበያ ያልወጣም የገበያ ዋጋ የለውም፤ የገበያ ዋጋ የሌለውም፤ በገበያ ዋጋ በገንዘብ አይተመንም፡፡ ስለዚህም በሪፖርት ከምናየውና ከሚነገረን ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን ገሚሱ የገበያ ዋጋ የሌለው ምናባዊ ስሌት ነው፡፡ የኑሮ መሐንዲሱ የኢኮኖሚ ባለሙያ ኑሮን ወደ ምናባዊ ስሌት ከወሰደው የህዝብ ገቢ መጠንና ኑሮም በገበያ ተለክቶ እውነቱ የሚታወቅ ሳይሆን ምናባዊ ይሆናል፡፡ አመለካከቱና አስተሳሰቡም የኑሮው ነጸብራቅ ነውና ኑሮውን ተከትሎ ምናባዊ ይሆናል፡፡ ሲያገኝም ሲያወጣም በምናባዊ ስሌት ነው፡፡

ሳይበላ የበላ መስሎ፣ ሳይጠጣ የጠጣ መስሎ፣ ሳይደላው የደላው መስሎ፣ ያላመነውን ያመነ መስሎ፣ ያልተቀበለውን የተቀበለ መስሎ፣ የናቀውን ያከበረ መስሎ፣ የጠላውን የወደደ መስሎ፣ በመታየት በምናባዊ ዓለም ውስጥ ይኖራል፡፡ ከኢሕአዴገ አባላት ውስጥ ጥቂቶቹ የጥቅም ተካፋይ ሲሆኑ አብዛኞቹ ግን በዚህ ምናባዊ ቀፎ ውስጥ እንደ ንብ የሰፈሩ ናቸው፡፡ ሕዝቡም በምናባዊ ዓለም ውስጥ የሚኖር ነው፣ የምክር ቤት ምርጫ ሊያደርጉ የወጡ ሰዎች በነጠላ ተሸፋፍነው የሆነ ያልሆነውን በትዝብት ተከታትለው የአስመራጮቹ ዓይን አስፈርቷቸው፣ ኢሕአዴግን መርጠው ቤታቸው ሲገቡ፣ የሚያውቋቸውን ታቦቶች ሁሉ እየጠሩ ኢሕአዴግን ንቀልልኝ ብለው የእርግማን መዓት ያወርዳሉ፡፡

ከመቶ ሚልዮን ሕዝብ ውስጥ ሁለት መቶ ሺሕ ሰው ሕንጻ ቢገነባ ከመቶ ሚልዮን ውስጥ ሦስት መቶ ሺሕ ሰው መኪና ቢገዛ አገር አደገች ማለት አይደለም፡፡ ብሔራዊ ሀብት በጥቂቶች በግል ይዞታ እየተሰረቀም ብሔራዊ ሀብት ሊሆን አልቻለም ተቆንጥሮ ተቆንጥሮ አልቋል፤ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ስሜትም ይሰረቃል፡፡ የኢትዮጵያውያን አገራዊ ስሜት ተሠርቆ አልቋል፡፡ ከገንዘብ ስርቆቱም በላይ ይኽ ስርቆት አገር እያጠፋ ነው፡፡

ሕዝቡ ከምናባዊ ዓለም ወጥቶ ገሃዱን ዓለም እንዲቀላቀል የኢኮኖሚ ባለሟል አለ ብሎ በወረቀት ላይ የሚጽፈውን ምርት ለሽያጭ ወደ ገበያ አውጥቶ፣ በገበያ ዋጋ አስተምኖ፣ እውነተኛውን በገበያ ዋጋ የተለካ የምርት መጠን አሳይቶ አለ ያለው መኖሩን ሊያረጋግጥ ይገባዋል፡፡ ገብረማርያምን የኃይለማርያምን አይተህ ተጽናና ማለት አይቻልም፡፡ አንጀት ላይ ጠብ የሚለው ሺዎች ለሚልዮኖች አስበው ሲሰሩ ሳይሆን ሚልዮኖች ለራሳቸው አስበው በገበያ ውስጥ ተወዳድረው እንዲሠሩ በተሟላ የመንግስት ቁጥጥር ድጋፍና አመራር የነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ሁኔታዎች ሲመቻቹላቸው ነው፡፡ “ጧት ጧት ደቧችንን ጠረጴዛችን ላይ የምናገኘው በዳቦ ጋጋሪው ጽድቅ ሥራ ሳይሆን ለራሱ ገንዘብ ለማግኘት ሲል በሚሠራው ሥራ ነው፤” ሲል የነጻ ገበያ ኢኮኖሚን ስውር እጅ አሠራር አዳም ስሚዝ አረጋግጧል፡፡ ከርሱ በኋላም ሌሎች ኢኮኖሚስቶች የብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አመራር የገበያውን ጉድለት እንዴት እንደሚቀርፍ አመልክተዋል፡፡ “ልማት ማለት አንድ ሰው ሊሆንና ሊያደርግ የሚፈልገውን ሕጋዊ ነገሮች የመሆንና የማድረግ ነጻነትና አቅም ሲያገኝ ነው፤” ሲሉ በ1998 በልማት ኢኮኖሚክስ የኖቤል ተሸላሚ የሆኑት አማርተያ ሴን ነግረውናል፡፡

ይኽን አይቶ መንግሥት የኢኮኖሚ ፖሊሲውን እንደገና ካልመረመረ የኢኮኖሚ አማካሪዎቹን ችሎታ ካልተጠራጠረ፣ የወረቀት ላይ ቁጥርን ብቻ ሳይሆን ገበያዎችን ተንትናችሁ ተርጉሙልኝ ካላላቸው ተያይዘን ገደል መግባታችን ነው፡፡ በፖለቲካው የተፈለገው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዓይነት ማዕከላዊ ዕቅድን እና ነጻ ገበያውን ማቀላቀል ቢሆንም የቅልቅሉን ዓይነት በብልሃት መምረጥ፣ ምናባዊ ዕቅድና ክንውኑን ብቻ ሳይሆን በገሃድ በዓይን የሚታየውን የገበያውን ሁኔታ መከታተል፣ ተነጣጥለው ለየራስ እየሄዱ ያሉትን ማዕከላዊ እቅድና ገበያውን ማቀናጀት ያስፈልጋል፡፡

የገበያውን ምልክትና ቋንቋ ያልተረዱ፣ ይኽ ከዚያ ይበልጣል ያ ከዚህ ያንሳል እያሉ ምናባዊ ቁጥር ገጣጥመው ማማለል የለመዱ፣ በምናባቸው አቅደው በምናባቸው የፈፀሙትን ማነጻጸር ብቻ የሚችሉ፣ ወደ ገበያ ወረድ ብለው ተጨባጭ ሁኔታን ያላዩ ቁጥር አምላኪ የኢኮኖሚ አማካሪዎች ገበያው በሽሚያ እርሾ እየቦካ መሆኑን ማየት ተስኗቸዋል፡፡ ሙያቸው ሰው እያስራበ፣ አያስኮበለለና እያስገደለ እንደሆነ አልተሰማቸውም፤ ልባቸው ደንድኗል፡፡

በምርጫ 2002 ፋሲካ ሰሞን አርባ ብር የነበረ የዶሮ ዋጋ በምርጫ 2007 ፋሲካ ሰሞን አራት መቶ ብር ከገባ በምርጫ 2012 ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል፣ በምርጫ 2007 ሚልዮኖች ከተሰደዱ በምርጫ 2012 ምን ያህል ሊሰደዱ እንደሚችሉ መገመት ያስቸግራል፡፡ ያሰቃየን ካይዘንን፣ ውጤት ተኮርን፣ ቢ.ፒ.አርን፣ ቢ.ኤስ.ሲ.ን አለማወቅ አይደለም፣ ያሰቃየን ደላላው አይደለም፡፡ ነጋዴውም አይደለም፡፡ ያሰቃየን የእነኚህ ሁሉ ገዢ ቃል የሆነው ገበያው ነው፡፡ እኛው ከውድድር ወደ ሽሚያ የለወጥነው ገበያው ነው፡፡

የበላን የበረሀ አሸዋ አይደለም፣ ባህርም አይደለም፣ ያረደንም ሰው አይደለም፡፡ የበላን ያረደን፣ ለስደት፣ ለስቃይ፣ ለሞት፣ ለዋይታ፣ የዳረገን ገበያው ነው፡፡ ሰው አገር ሞልቶና ተርፎ እኛ አገር የጠበበውና የተኮማተረው መኮማተሩንም ራሱን ሳይደብቅ የሚነግረን በመንግስት አስተዳደር ሳጥን ውስጥ ታስሮ ያለው የሥራና የእንጀራ ገበያ ነው፡፡ በአዋጅና በሕግ ስለተደነገገው ገበያ እንደ ካይዘኑ፣ እንደ ውጤት ተኮሩ፣ እንደ ‹ቢ.ፒ. አሩ›፣ እንደ ‹በ.ኤስ.ሲው› ልናውቅ ልናጠና ባለመፈለጋችን በኑሮ ተቀጣን እየተቀጣንም ነው፡፡ ገበያው ሰማይ ይሰቅለናል፤ መቀመቅ ያወርደናል፤ ገበያው ያሰድደናል፤ ያስገድለናል፤ ጥቂቶችንም ገበያው ያንቀባርራል፤ ያንደላቅቃል፤ ያመጻድቃል፡፡

የሚጻፉትን ቁጥሮች እና የገበያውን ምልክት በማያገናዝቡ፣ የኛን የምርትና የሸመታ ምርጫ ሥነልቦና በማያውቁ፣ እኛ በገበያዎቻችን ውስጥ ልናገኛቸው የምንፈልጋቸውን የሸቀጦች ዓይነት በማይረዱ ባዕዳን አማካሪዎች እገዛ ምክርና ትዕዛዝ ገበያውን ማየትና የገበያውን ቋንቋ መስማት በተሳናቸው የአገር ውስጥ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ጓዳ ውስጥ በማዕከል ታቅዶ የሚተገበር ፖሊሲ ጎደሎ ነው፡፡ የውጭውን አገር ጽንሰ-ሐሳብና ልምድ ብቻ ይዞ ምድሩ ሳይታወቅ ሰማይ መቧጠጥ ነው፡፡ በሰው አገር ዕድገት ሞዴል ጉጉት ናፍቆትና ምኞት ራስን መደለል የልማትን ትርጉም ሳያውቁ ልማታዊ ነኝ ማለት የሕዝብ ሕይወትና ኑሮን የሙከራ ጊዜ ማድረግ ነው፡፡ ለአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታና ለህዝቡ ሥነልቦና በቂ ትኩረት አለመስጠት ነው፡፡

ቁጥር ብቻ እየታየ የሸማቹን አቅም ለመገንባት የሚረጨው የጥሬ ገንዘብ መጠን ወደኋላ ተኩሶ ዋጋን በማናር ጀርባችንን አቁስሎታል፡፡ የአምራቹን አቅም ለማሳደግ ለጥቂቶች የሚሰጥ ያዝ ለቀቅ ድጋፍ ግብታዊ እርምጃም ነቀዝ ፈልፍሏል፡፡ ከቁጥር ቁማር ወጥተን ከፈጠርነው አርተፊሻል የሽሚያ ገበያ ተላቀን የገበያ ኢኮኖሚውን እና የልማት ኢኮኖሚውን ካላመጣጠን ላንነሳ ተሰናክለን እስከምንወድቅ ኑሯችን የአቦ ሰጥ እንደሆነ ይቀጥላል፡፡ በአቦ ሰጥ ይገኛል በአቦ ሰጥ ይታጣል፡፡

የነጻ ገበያ ኢኮኖሚ አወቃቀርና አካሄድ በውስጣዊ ኃይላት እቅስቃሴ የሚመራ ሥርዓት ነው፡፡ ላለመሰቃየት፣ ላለመሰደድ ላለመሞት ላለማልቀስ በአቦሰጥ ላለመኖር ከሽሚያ ገበያና ኑሯችንን ቤተሙከራ ከማድረግ ወጥተን ትክክለኛውን የነጻ ገበያ ሥርዓት መዘርጋትና የሥርዓቱን ውስጣዊ ኃይላት እንቅስቃሴ ማወቅና መጠቀም ያስፈልጋል፡፡

በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ሦስት እጥፍ ያደገ ኢኮኖሚ
***

ከላይ በእንቆቅልሽ መልክ በተመለከተው የአገር ውስጥ ጥቅል ምርት ዕድገት የሕዝቡን የኑሮ ደረጃ በማሻሻል ረገድ ፋይዳ ቢስ መሆኑን በገበያ መገለጫ ያረጋገጥን ቢሆንም በስታቲስቲካዊ መረጃውም የተሳሳተ እንደሆነ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ብዙ ኢትዮጵያውን ስለ ኢኮኖሚው የመንግስትን መረጃ ፈጽሞ እንዳያምኑ ካደረጋቸው ምክንያቶች አንዱና ዋናው የጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ዕድገት ተብሎ የሚጠራው ነው፡፡ ገበያ ውስጥ ምርት ጠፍቶ ዋጋው በየጊዜው ከሚገባው በላይ ወደላይ እየተሰቀለ ምርቱና አቅርቦቱ በየዓመቱ በዐሥራ አንድ በመቶ አደገ ሲሉ ሕዝቡ ታዲያ እንዴት ይመናቸው?

ይኽ በፍጥነት አደገ የሚባል ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን የሕዝቡን ዓመታዊ ነፍስ ወከፍ ገቢን ከልክ በላይ አሳድጎ፣ በድህነት ቅነሳ መለኪያ አመልካች የሕዝቡ ኑሮ ደረጃ የተለወጠ በማስመሰል ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰው ሆኖበታል፡፡ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት በዓመት በአገር ውስጥ በሚኖሩ ሰዎች በገበሬው፣ በወዛደሩ፣ በፀጥታ አስከባሪው፣ በመከላከያ ሠራዊት አባሉ፣ በዳኛው፣ በጋዜጠኛው፣ በመምህሩ፣ በሐኪሙ፣ በቢሮ ሠራተኞች፣ በነጋዴው፣ በሙዚቀኛው፣ በፀጉር አስተካካዩ፣ በቤት ሠራተኛው፣ በሾፌሩ፣ በዘበኛው በጫማ አሳማሪው በዳንስ አስተማሪው በጭፈራ ቤት ሥርዓት አስከባሪው ወዘተ. ተመርቶ በሸቀጥ መልክ ለገበያ የቀረበ ወይም ለገበያ እንደቀረበ ተቆጥሮ ዋጋው የተተመነ ቁሳዊ ዕቃና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት ነው፡፡

ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት በገንዘብ ዋጋ በኹለት መልክ ይለካል፡፡ አንዱ ምርቱ በተመረተበት ዓመት የገበያ ዋጋ መለካት ሲሆን፣ ኹለተኛው የዋጋ ንረትን በምርቱ ልኬት ውስጥ ላለማስገባት በአንድ በተመረጠ ዓመት ቋሚ ዋጋ አማካኝነት የተከታታይ በርካታ ዓመታት ምርት መጠንን መለካት ነው፡፡ ምርቱ በተመረተበት ዓመት የገበያ ዋጋ የተለካ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን የየዓመቱን የዋጋ ንረቶች ስለሚጨምር እርግጠኛው የምርት መጠን አይደለም የዋጋ ንረቱ አሳብጦታል፡፡ ይኽ በዋጋ ንረት ያበጠ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ምስለ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት (Nominal GDP) ይባላል፡፡

በሌላ በኩል እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት (Real GDP) በተመረጠ ዓመት ቋሚ የገበያ ዋጋ የተለካ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን ሲሆን በየዓመቱ የሚከሰተውን የዋጋ ንረት ስለማይጨምር በዋጋ ንረት ሳይበከል የተተመነ ምርት መጠን ነው፡፡ አንድ ገበሬ አምና ስምንት ኩንታል ስንዴ አምርቶ እያንዳንዱን ኩንታል በአንድ ሺሕ ብር ቢሸጥ የስምንት ሺሕ ብር ምርት አመረተ ማለት ነው፡፡ ዘንድሮ ዐሥር ኩንታል ምርት አምርቶ እያንዳንዱን ኩንታል በሺሕ ኹለት መቶ ብር ቢሸጥ የዐሥራ ሁለት ሺሕ ብር ምርት አመረተ ይባላል፡፡

የአምናው ኩንታል ምርት በአንድ ሺሕ ብር ዋጋ ተለክቶ የዘንድሮው ኩንታል ምርት በሺሕ ሁለት መቶ ብር ዋጋ መለካቱ የዘንድሮውን ምርት የዋጋው ንረት አሳብጦታል፡፡

የአምናው ስምንት ኩንታል ምርትና የዘንድሮው ዐሥር ኩንታል ምርት በተመሳሳይ የአምና ቋሚ ዋጋ አንድ ሺሕ ብር ቢለኩ ገበሬው ዘንድሮ ያመረተው ምርት መጠን ዐሥራ ኹለት ሺሕ ብር ሳይሆን ዐሥር ሺሕ ብር ነው፡፡ በአምናው ቋሚ ዋጋ የተለካው የዘንድሮ ምርት መጠን በዋጋ ንረት አልተበከለም፡፡ እርግጠኛውን የምርት መጠን ለመለካት የአገር ውስጥ ምርት መጠን በአንድ በተወሰነ የቀድሞ ዋጋ መሠረት ይለካል፡፡ የቀድሞዎቹን ዓመታት ትተን የቅርብ ጊዜ መረጃዎችን ብቻ ብንወስድ፣ በኢትዮጵያ ከ1992 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2003 ዓ.ም. ድረስ የየዓመቱ እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት በ1992 ዓ.ም. ቋሚ የገበያ ዋጋ ሲለካ ቆይቷል፡፡ ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ ግን ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን መለኪያ ወደ 2003 ዓ.ም. ቋሚ የገበያ ዋጋ ተከልሷል፡፡

ይኽ የሚሆንበት ምክንያትም ዋጋ ሳይከለስ ለረጅም ጊዜ ቢቆይ ትክክለኛውን የምርት መጠን ስለማይለካ ነው፡፡ ስለሆነም ሁሉም አገራት ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ የምርት መለኪያ ዋጋ ዓመታቸውን ይከልሳሉ፡፡ ኢትዮጵያ ኬንና ናይጄሪያ መከለሳቸውን ከዚህ ቀደም አይተናል ኢትዮጵያ ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዛሬ ባሉት ዓመታትም እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት እየተለካ ያለው የ1992ቱን ዓ.ም. መለኪያ ዋጋ በ2003 ዓ.ም. ቋሚ የገበያ ዋጋ አማካኝነት በመከለስ ነው፡፡ የዚህ እንድምታ ምን እንደሆነ ቀጥለን እንመልከት፡፡

በጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን መለኪያ ቋሚ ዋጋ ከ1992 ወደ 2003 ዓ.ም. መከለስ ምክንያት የ2003 ዓ.ም. እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን ከ1992 እስከ 2003 በነበሩት የየዓመታቱ ዋጋ ንረቶች ተበክሎ አብጧል፡፡ ስለሆነም በዋጋ ንረት ተበክሎ በማበጥ አራት መቶ ሰባ ቢልዮን ብር የሆነው የ2003 ዓ.ም. እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን በ1992 ዓ.ም. ቋሚ ዋጋ የተለካውን አንድ መቶ ሐምሳ ስምንት ቢልዮን ብር የ2003 ዓ.ም. እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ሦስት ነጥብ ሦስት እጥፍ ሆኗል፡፡ ነፍስ ወከፍ ገቢም ከአንድ ሺሕ ዘጠኝ መቶ አርባ ስድስት ብር ወደ ስድስት ሺሕ ኹለት መቶ ስልሳ ሰባት ብር አብጧል፡፡

የግብርናው የኢንዱስትሪውና የአገልግሎት ዕድገቶችም አብጠዋል፡፡ በዚህም መሠረት ስልሳ አምስት ቢልዮን ብር የነበረው የግብርና ምርት ወደ ኹለት መቶ ዐሥራ ሦስት ቢልዮን ብር፣ ሃያ አንድ ቢልዮን ብር የነበረው የኢንዱስትሪ ምርት ወደ ሐምሳ ቢልዮን ብር፣ ሰባ ሦስት ቢልዮን ብር የነበረው የአገልግሎት ምርት ወደ ኹለት መቶ ሰባት ቢልዮን ብር አብጠዋል፡፡ የሕዝቡ ኑሮ የአዲሱን ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን ያህል ሦስት እጥፍ አደገ ማለት ነው ወይስ ለቆጠራ ያህል ብቻ የሚያገለግል የወረቀት ላይ ዳማ ጨዋታ ነው? ጥያቄ የሚያጭር ጉዳይ ነው፡፡

የአገር ውስጥ ምርቱ መለኪያ ቋሚ ዋጋ ከ1992 ወደ 2003 በመቀየሩ ምክንያት በወረቀት ላይ በሚጻፉ ቁጥሮች ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ቅጽበታዊ ሦስት እጥፍ ጭማሪ ነፍስ ወከፍ ገቢን ማሳደግና ድህነትን መቀነሰ ይቻላል ማለት ነውን፡፡ ይኽ የአገር ውስጥ ጥቅል ምርት መጠን ሳያድግ በዋጋ ንረት አማካኝነት ያደገ መምሰል ብዙ እንድምታዎች አሉት፡፡ የአገር ውስጥ ምርት ዕድገቱን መሠረት አድርገው የሚለኩ ሌሎች የሰውና ኢኮኖሚ ልማት መረጃዎች የተዛቡ ይሆናሉ፡፡ የዋጋ ንረትም በከፍተኛ ደረጃ የጨመረው ከዚህ ዓመት ጀምሮ ሲሆን መንግሥትም በዋጋ ንረቱ ምክንያት ለመሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች ድጎማ ለማድረግ ስንዴ፣ ዘይትና ስኳር በውጭ መንዛሪ እያስገባ ማከፋፈል የጀመረው በዚሁ ዓመት ነው፡፡

ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ሁሉም አገሮች በተወሰኑ ዓመታት እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን መለኪያ ቋሚ ዓመተ ምሕረቱን ይከልሳሉ፡፡ በተባበሩት መንግሥታት የብሔራዊ ኢኮኖሚ ልኬት መርህም ተቀባይነት ያለው አሠራር ነው፡፡ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠኑን ያሳበጠው የቋሚ መለኪያ ዓመቱ መከለሱ በራሱ ሳይሆን ከክለሳው በፊት የነበሩት እጅግ ከፍተኛ የዋጋ ንረቶች በክለሳው ውስጥ በመካተታቸው ነው፡፡ የዋጋ ንረት በኹለትና በሶስት በመቶ ብቻ በሚቆጠር መጠነኛ በሆነበት ኢኮኖሚ ውስጥ የመለኪያ ቋሚ ዓመቱ መከለስ ብዙ ለውጥ አያስከትልም፡፡ የዋጋ ንረት ከፍተኛ በሆነበት ኢኮኖሚ ውስጥ ግን የመለኪያ ቋሚ ዓመት ክለሳው የአገር ውስጥ ምርት መጠንን ከልክ በላይ ያሳብጠዋል፡፡

በቋሚ መለኪያ ዓ.ም. ክለሳው ምክንያት ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት እና ዓመታዊ ነፍስ ወከፍ ገቢ በወረቀት ላይ በሚታይ ቁጥር ደረጃ ወደ መካከለኛ ኑሮ ደረጃ በፍጥነት እየተጠጉ ነው፡፡ ድህነትም በፍጥነት እየቀነሰ ነው፡፡ አብዛኛው ሕዝብ ግን በዋጋ ንረት ምክንያት ኑሮው በማዘቅዘቁ ከመካከለኛ ኑሮ ደረጃ እየራቀ እየደኸየም ነው፡፡ ወረቀቱ ነው ስለኑሯችን የሚመሰክረው ወይስ የገሃዱ እውነታ ነው? የየዓመቱ ገደብ የለሽ ዋጋ ንረቶች ለአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጭንቀቶችና ስቃዮች ናቸው፡፡ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርትን እና ዓመታዊ ነፍስ ወከፍ ገቢን በፍጥነት አሳድገው በፍጥነት መካከለኛ ገቢ ውስጥ ለማስገባት ድህነትንም ለመቀነስ ሩቅ ዓልመው ሩቅ ለማደር ለሚተጉት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ባለሙያዎች በደስታ ጮቤ የሚያስረግጡ ናቸው፡፡ የጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን መለኪያ ዓ.ም. በየዐሥር ዓመቱ ስለሚከልሱት በ2013 እንደገና ተከልሶ የምርት መጠኑና ነፍስ ወከፍ ገቢው ሦስት እጥፍ አድገው እንደታለመው በቅርብ ዓመታት ድህነትን ለማጥፋት ወደ መካከለኛ ገቢ መጠን መቃረብም ይቻላል፡፡

በ1980ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት የኢትዮጵያ እርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ዐሥር ቢልዮን ብር ገደማ ነበር፡፡ የ2003 ዓ.ም. አራት መቶ ስልሳ ዘጠኝ ነጥብ አምስት ቢልዮን ከ1980ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት ዐሥር ቢልዮን ብር አካባቢ ጋር ሲነጻጸር ሐምሳ እጥፍ ግድም እንደሆነ ይታያል፡፡ በ2008ም ሰባት መቶ አርባ ሰባት ቢልዮን ብር ስለደረሰ ሰባ እጥፍ ደርሷል፡፡ ይኸ ዕድገት በእርግጠኛ የአገር ውስጥ ምርት ስሌት ሲሆን በምስለ የአገር ውስጥ ምርት ስሌትም በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ ከሃያ ቢልዮን ብር በታች የነበረው ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ወደ ኹለት ተሪልየን ብር እየተቃረበ ስለሆነ ከመቶ እጥፍ በላይ አድጓል፡፡

እንግሊዝ በኢንዱስትሪ አብዮቷ ዘመን ኢኮኖሚዋን እጥፍ ለማድረግ ስልሳ ዓመታት ፈጅቶባታል፡፡ አሜሪካ በ19ኛው ክፍ ለዘመን መጨረሻ ገደማ ኢኮኖሚዋ መመንጠቅ ሲጀምር ኢኮኖሚዋን እጥፍ ለማድረግ ሐምሳ ዓመታት ፈጅቶባታል፡፡ በፍጥነት ያደጉት የምሥራቅና ደቡብ ምስራቅ እስያ አገራትም ኢኮኖሚያቸውን እጥፍ ለማድረግ እስከ ዐሥር ዓመታት ፈጅቶባቸዋል፡፡ የእኛን አገር ኢኮኖሚ ዕድገት ከነዚህ አገራት እድገት ታሪክ ጋር ስናነጻጽር የኤሊና የጥንቸል ሩጫ ውድድር ይመስላል፡፡ እነርሱ ኤሊዎቹ እኛ ጥንቸሏ ነን፡፡ ይህ የሚታመን መረጃ ነውን በኢኮኖሚ ጥናት ሳይንስ ሊረጋገጥ ይችላልን፡፡

እንደ የዓለም ባንክ፣ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት፣ ዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ድርጅት፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የመሳሰሉ የዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ሁኔታውን ያውቃሉ ወይስ አያውቁም? አውቀውስ ተቀበሉት ወይስ አልተቀበሉትም? አሳምረው ያውቃሉ፡፡ ከማወቅም አልፎ አምነው ተቀብለው መዝግበውታልም፡፡ የአገራትን መረጃዎች አጣጥለው በዚህ ሳቢያ በትውውቅና በሹመት የተገኘ ሥራቸውንና ወፍራም ደመወዛቸውን ከሚያጡ አዎን ብለው አጨብጭበው መቀበሉን ይመርጣሉ፡፡ ማን ለማን መስዋዕት ይሆናል? የተከበሩት ፈረንጆች የሙስና ተማሪዎች ሳይሆኑ አስተማሪዎች እየሆኑ ነው፡፡

አገራትም አንዱ የሌላውን መረጃ ለማጣጣልና ላለመቀበል ወኔው የላቸውም፡፡ ከሶቭየት ኅብረት መውደቅና ከቀዝቃዛው ጦርነት ፍጻሜ በኋላ የመጣ ተቻችሎና ተግባብቶ የመኖር የዓለም ዐቀፍ ድርጅቶችና መንግሥታት ዘይቤ ነው፡፡ ይኽ የድርጅቶችና የመንግሥታት መቻቻል የታዳጊ አገራት ሕዝቦች ድህነት ይብቃን የሚያጠግቡን ይምሩን እንዳይሉ አደረጋቸው፡፡ መገናኛ ብዙሃን በእጃቸው በሆነ ባለሥልጣናትና የዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ሹማምንት የታዳጊ አገራት ድሃ ድምጻቸው ተቀማ፡፡ ከምዕራባውያን ጋር ተስማምተው እስከኖሩ ድረስ ሕዝባቸውን ቢያስርቡም ባያስርቡም ጉዳዬ ነው የሚል ጠፋ፡፡ ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶቹ እንደውም ለውጭ ኢንቬስተሮች ሁኔታዎች ይመቻቹ እንጂ የማያውቁትን ለመመስከር መጽሐፍ ቅዱስ ይዘውም ቢሆን ይምላሉ፡፡

ኢትዮጵያ በራሷ እምነትና መንገድ ኢኮኖሚዋን በዚህን ያህል መጠን አሳድጌአለሁ ብላ ብትል፣ ይኽ አለካክ ትክክል አይደለም የሚልና የሚያጣጥለው የትኛው የሕዝብን ጉዳይ ከራሱ ጥቅም የሚያስቀድም ዓለም ዐቀፍ ድርጅት ወይም አገር ነው? በጥቂቱም ቢሆን ወኔው ያላቸውና መጻፍ ካስፈለጋቸው የሚጽፉትና በሳይንሳዊ መንገድ የሚተነትኑት አንዳንድ ታዋቂ የኢኮኖሚክስ ጥናት ተመራማሪ ዩኒቨርሲቲዎች እና የአንድ አገር ኢኮኖሚ ተመራማሪ ግለሰቦች ናቸው፡፡