በአርባ ምንጭና አካባቢዋ ከፍተኛ ውጥረት መንገሱ ተሰማ፡፡የህወሃት ታጣቂዎችና ህዝቡ ተፋጠዋል፡፡

በአርባ ምንጭና አካባቢዋ ከፍተኛ ውጥረት መንገሱ ተሰማ፡፡የህወሃት ታጣቂዎችና ህዝቡ ተፋጠዋል፡፡

በአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ በሻራ ከተማ ሶስት ሰዎች በአጋዚ ወታደሮች መገደላቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡በዚህ የተበሳጨው ህዝብ አደባባይ ወጥቶ ተቃውሞ እያሰማ ነው፡፡

ይድረስ

ለኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚንስትር ለተከበሩ ለዶ/ር አብይ አህመድ

ስላለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ብቻ ሳይሆን ስላለፉት 20ና ከዚያ በላይ ስለሆኑ ዓመታቶች ሲባል አርባ ምንጭ ይመጡ ዘንድ ጥሪ እናቀርብሎታለን፤ እንጠብቆታለንም!!!

ጥሪና ጥበቃችን የጨለምተኝነት፣ የተቃዋሚነት፣ ወይም ደግሞ ብልጥ ልጅ እየበላ ያለቅሳል ዓይነትን ሆኖብን ሳይሆን ስለሚታይና ስለሚጨበጥ ሃቅ ሲባል፤ ስለመኖርና ስላለመኖር (የህልውና) ጉዳይ ሆኖብን ነውና በቅድሚያ ይህንን ይረዱ ዘንድ በአክብሮት እንጠይቆታለን፡፡

እናም እንዲመጡ ስንጠይቆት አያሌ ምክንያቶች ስላሉን ነው፡፡ ጥቂቶቹ

አርባ ምንጭ ….

ተፈጥሮዋ (የእግዚአብሔር እጅ) ዘብ ሆኗት እንዳትወድቅና እንዳትጠፋ ቢያደርጋትም አይደለም አዳዲስ ነገሮች በከተማዋ ሊሰሩባት ይቅርና ባለፉት ጨቋኝና አምባገነን ናቸው ተብለው በተፈረጁ መንግስታቶች ጭምር ተሰርተዋል ተብለው የተቀመጡ ሃብቶቿ ውስጣቸው እንዲጠፋ፤ ባዶና ቀፎአቸውን ብቻ እንዲቀሩ ተደርገዋል፡፡ ሀይቆቿ፣ ምንጮቿ፣ ፓርክና ዕሴቶቿ አደጋ ላይ ወድቀዋል እየከሰሙም ይገኛሉ፡፡

በፌደራል መንግስት ጭምር ቃል የተገቡልን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎቻችን በማይታወቁ ሁኔታዎች ሳይተገበሩ ቆይተዋል፤ የውሃ ሽታም ሆነው ቀርተዋል፡፡ በትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የተካተቱ ተግባራት ጭምር እንዲሰረዙና እንዲቀለበሱ ተደርገዋል፡፡ አንድ መንገድ ከተሰራ ዘመንን ፈጅቶና ህዝቡን አስጩሆ ነው፡፡

ውሃ ላይ ቁጭ ብለን ውሃ ይጠማናል፤ ምግብ ላይ ተቀምጠን ምግብ ይርበናል፡፡

ከተማዋ ከልማትና መልካም አስተዳደር ውጪ ከመሆኗ የተነሳ በተለያየ መልኩ (“ተባብረው ካስተኟት ከተማ ጀምሮ ….”. ) ብዙ ወጣቶች፣ ምሁራንና፣ ነጋዴዎች በፅሁፋቸው፣ በቃላቸውና፣ በእንቅስቃሴዎቻቸው ሁሉ ድምፃቸውን አሰምተዋል፡፡ ጮኸዋል፡፡ ታስረዋል፣ ሞተዋልም፡፡

አያሌ ወጣቶቿ በስራ ሳይሆን በአልባሌ ቦታዎች ላይ እንዲውሉና እንዲጠፉ ተደርገዋል፡፡

ህዝብ ከመጀመሪያው ምርጫ ማለትም ከ1987 ዓ.ም ጀምሮና ከዚያ በኋላ በተደረጉት ቀጣይ ምርጫዎች ሁሉ ተቃውሞውን ሲገልፅባት ቆይቷል፡፡

ውድቀቷን ማየት አሻፈረን፣ ስራ አገኝተን መስራት አቃተን ያሉ አያሌ ወጣቶቿ በከተማዋ፤ ከከተማዋም አልፈው እስከ ኤርትራ በረሃ ድረስ በመሄድ እንዲሞቱ ተደርገዋል፡፡

ምንጩ ባልታወቀ አካሄድ ከባለስልጣኖች ጋር በመመሳጠርና አጋር በመሆን ብቻ ትላንትና ባዶ የነበሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ዛሬ ባለ ሚሊየነሮች ሆነዋል፡፡ የህዝብ ሃብት በጥቂቶች ቁጥጥር ውስጥ እንዲውል ተደርጓል፡፡

ሲፈልጉ ባለስልጣኖችን ማውጣት የሚችሉ፣ ሲፈልጉ ደግሞ ማውረድ የሚችሉ፣ ሲፈልጉ የህዝብን ልጆች መግፋትና ማሰደድ የሚችሉ፣ ለህዝብና ለአካባቢ መወገን የቻሉ አመራሮችን፣ ምሁራኖችንና፣ ነጋዴዎችን ነጥለው ማጥቃትና ከፖለቲካው መስመር ከተቻለም ከከተማው ለማጥፋት ምንም የማይሳናቸው ሃይ ባይ የለሾች፣ እጃቸው የረዘመባቸው፣ ክንዳቸው በረዘመው እጃቸው የፈረጠመባቸው የአንጃና የማፍያ መሰል ኃይሎች በከተማዋ ተደራጅተውባታል፡፡

ስርዓት አልበኝነት፣ ማንአለብኝነትና ተጠያቂ አልባነት ነግሰውባታል፡፡ መሬት ይሰረቃል፣ በአድልኦና በሙስና ይከፋፈላል፡፡ ነዋሪውና ሰፊው ህዝብ ግን ባይተዋር ሆኖ ይመለከታል፡፤

ከተማዋ የዱርዬዎች፣ የነጥቆና ሰርቆ አደሮች፣ የከፋፋዮችና የደላሎች መፈንጫ ሆናለች፡፡

የአምቦ ህዘብ እየጠየቀ ካለው የመብት ጥያቄ ብሎም ይህን አሳካለው ብሎ ከወሰደው የትግል አካሄድ ባልተናነሰ ሁኔታ አርባ ምንጭም ብዙ ጥያቄዎችን ስትጠይቅ ቆይታለች፡፡ የነፍጠኛ ከተማ በሚል ዳር እንደትይዝ፣ የአሸባሪዎች መነሃሪያ ተብላ አንድትፈረጅና በጎሪጥ እንድትታይ ተደርጋለች፡፡

በቅርቡ የኦሮሞ ወይም የአማራ ህዝብ አደባባይ ወጥቶ ከመጮሁ አስቀድሞ የአርባ ምንጭና መላው የዞናችን ህዝቦች አደባባይ በመውጣት ስለ መብት፣ ስለእኩል ተጠቃሚነት፣ ስለ ዳርና ድንበር፣ ስለ ህገወጥ የሀብት ዘረፋ፣ ስለኢትዮጵያዊነት፣ ስለ አጠቃላይ የሀገር ህልውና ሲጮሁ ቆይተዋል፡፡

የጋሞ ህዝብ ….

ማንነቱን፣ አካበቢውንና፣ ህዝቡን ያከበረ አመራር በአግባቡ እንዳይሰራለት ዕድሜውን የማሳጠር ስራ ይሰራበታል፡፡

በኢህአዴግ የሚመራው መንግስት ያስቀመጣቸው የብሔር፣ የብሔረሰቦችና፣ የሕዝቦች እኩልነትና ተጠቃሚነት የመብት ጥያቄዎች ለግለሰቦች መነገጃ እንደ አጋጣሚ ከመሆናቸው ውጪ ለተጮቀነውና ልማትን ለተጠማው ህዝባችን አንዳች እንዳይሆኑ ተደርገዋል፡፡

ኢህአዴግ ታግዬ፣ ደምቼና፣ ሞቼ ምላሽ ሰጥቻለሁ እያለ ሲናገር የምንሰማቸው የማንነት፣ የባህልና፣ የቋንቋ ጥያቄዎች በጋሞ ብሔር ላይ ከበፊቶቹ ስርአቶች በከፋ መልኩ በመጥፎ ሁኔታ እንዲፈፀሙና ስላቅ እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡ ዕሴትና ሃብቱን በጠራራ ፀሐይ ተዘርፏል፡፡ ተቀምቷልም፡፡ ዳርና ድንበሩ ተሸራርፈውበታል፡፡

የጋሞ ህዝብ እያለ የለህም ተብሎ መፅሐፍ እንዲፃፍበት ተደርጓል፡፡ ስድብና ጥላቻ ደርሰውበታል፡፡

የጋሞ ህዝብ ለዘመናት በቆየበት አንድነትና ፍቅሩ አብሮ እንዳይኖር፤ ተለያይቶ እንዲበታተን፤ አያሌ ቁማሮች፣ ሴራና፣ በደሎች ፖለቲካውን ሽፋን ባደረጉ አመራር ነን ባዮች ተፈፅመውበታል፡፡ ይህን የተቃወሙ ወጣቶች፣ ምሁራንና ነጋዴዎች ታሰረዋል፣ተፈርጀዋል፣ ተሰደዋል፣ ሀብትና ንበረታቸውን፣ እድልና አጋጣሚዎቻቸውን እንዲያጡ ተደርገዋል፡፡ ዛሬም ድረስ ምንም የማያውቁ የሃገር ሽማግሌዎች (ተሰድበውና መፅሐፍ ተፅፎባቸው ሳለ) ጥያቄ በማቅረባቸው ብቻ በፍርድ ቤት ቀጠሮ እንዲመላለሱ ተደርገዋል፡፡ ብዙዎች በምህረት አዋጅ ይቅር በተባሉባት ሃገር የመብት ጥያቄ አቅራቢዎች ፍርድ ቤት ዛሬም ድረስ እንዲመላለሱ መደረጋቸው ምን ያህል ከፌደራል መንግስቱ የተቃርኖ ስራ በዚህ ህዝብና አካባቢ ላይ እንደሚሰራ ይህ ጥቂቱ ማሳያ ይሆናል፡፡

ህዝብን በመበታተንና ማንነትን በማዳከም ስትራቴጂ በተወሰኑ የዞኑ አካባቢዎች ወረዳዎችን ከወረዳዎች፣ ቀበሌዎችን ከቀበሌዎች የሚያስተሳስሩ መንገዶች እንዳይኖሩ ተደርገዋል፡፡ ጥራት ያለው መንገድ ማግኘትም የህልም እንጀራ ሆኗል፡፡

በጉዞ ህዝብ ለአላስፈላጊ የገንዘብ፣ የጊዜና፣ የጉልበት ወጪዎች እንዲዳረግ ተደርጓል፡፡

የህዝብን ቁጥርና የቦታ አሰፋፈር/ርቀት/ ባላገናዘበ መልኩ በንፁህ የመጠጥ ውሃ፣ በመብራትና፣ በትምህርት፣ በሌሎች የመሰረተ ልማት መስኮች ህዝብ ወደ ኋላ እንዲቀር ተደርጓል፡፡

ህዝብ የማያውቃቸው፣ ያልመረጣቸውና፣ ቅሬታም ያቀረበባቸው አካላት በጉልበት በህዝብ ጫንቃ ላይ እንዲቀመጡ ተደርገዋል፡፡

በዳዮች ከመጠየቅ ይለው በስልጣን ላይ ስልጣን፣ በወንበር ላይ ወንበር እንዲሸለሙ ተደርገዋል፡፡ ይባስ ተብሎ ለነገ ለማንሰራራት በሌላ ቦታ አድፍጠውና ተደራጅተው ተቀምጠዋል፡፡

የጋሞ ህዝብ በሃብቶቹ ባይተዋርና ገለልተኛ እንዲሆን፣ በስነልቦናም እንዲጎዳ ተደጓል፡፡

ባይሳካላቸውም የጋሞ ህዝብ ከወንድሙ የጎፋና የወላይታ ህዝቦች ጋር ፀብ እንዲሆን እንዲጣላና የጎሪጥ እንዲተያይ ተደርጓል፡፡ ፍቅርንና አብሮነትን ከመሰበክና ከመናገር ይልቅ ጥላቻና መበላለጥ በትውልዱ ላይ እንዲዘራ ተደርጓል፡፡

ቀጣዩ ጥሪዬ

ለተከበሩ የደኢህዴን ሊቀመንበር፤ የግብርናና እንስሳት ሃብት ልማት ሚንስቴር ሚንስትር ለአቶ ሺፈራው ሽጉጤ ሲሆን ጥቂት ነገርን ብቻ ልሎት አፈልጋለሁ፡፡

ለትውልዱ መልካም የሆነ አሻራን ያስቀምጡ ዘንድ ዕድል በእጆት ላይ ወድቃለች፡፡ ለዚህም እንኳን ደስ አሎት በቅድሚያ ልሎት እወዳለሁ!!!

የተከበሩ ሚንስትር የደቡብን ችግር ይበልጥ ደግሞ የጋሞ ጎፋ ዞንን ለእርሶ ማውራት ለቀባሪ የማርዳት ያህል ነውና ትላንትና ችግሩን እያወቁም ቢሆን ለማሰተካከል አቅም ባይኖሮትም ዛሬ አቅሙን አግኝተዋልና ክልሉን እየመራ ያለውን ድርጅቶትን /ደኢህዴንን/ ከጽ/ቤት ጀምሮ በማጥራት ህዝብ ለሚጠይቃቸው የህልውናና የመብት ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ይስጡ፡፡ 27 ዓመት ሙሉ ጥቂት ሰዎች ብቻ እንደፈለጋቸው የህዝብ ተወካይና የህዝብ ተጠሪ የሆኑበትን የሻገተ አሰራር ይለውጡት፣ ያዘምኑት፡፡ የክልላችንን ዳርና ድንበር ይበልጥ ደግሞ በነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ በኩል ያለውን ዛሬ ላይ በጉጂና በጌዲኦ፣ ብሎም በአማሮ ኬሌ አካባቢ የሚከሰቱ ችግሮችን መልክ ያስይዙ፣ ያስከብሩም፡፡ ወደ ነበሩበት የሚመለሱበትን ሁኔታንም ይፍጠሩ፡፡ በተመሳሳይም በኮንሶ አካባቢ ስለተፈጠሩት የህዝብ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ይስጡ፡፡ በመጨረሻም የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚንስትር የተከበሩ ዶ/ር አብይ አህመድን ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ይጋብዙልን፡፡ አርባ ምንጭም እንዲመጡ የበኩሎትን ይወጡልን፡፡

በመጨረሻም በተፈጥሮ ወደታደለችው፣ ዕፁብ፣ ድንቅና ማራኪ ወደ ሆነችው፣ ወደ የጥበብ ምድሯ ወደ አርባ ምንጭ እንኳን ደህና መጣችሁ ለማለት ያብቃን፤
እያልኩኝ፡፡

በመጨረሻ መጨረሻም

የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚንስትር የተከበሩ ዶ/ር አብይ አህመድ በቀጣይና በአጭር ጊዜ ውስጥ አርባ ምንጭ እንዲመጡ በታላቅ አክብሮት ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡ እንጠብቆታለንም፡፡

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!