የወሎ ሙስሊሞችን ቁስል የነካካው የአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ስብሰባ!!! (በዘሪሁን ገሠሠ)

 የወሎ ሙስሊሞችን ቁስል የነካካው የአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ስብሰባ!!! (በዘሪሁን ገሠሠ)
.
<< …በሙስሊም በመሆኔ ብቻ “አሸባሪ” ተብዬ ከፍተኛ ድብደባ ተፈፅሞብኛል፡፡ በገመድ አስረው ሸንተውብኛል፡፡ ጣቶቼ ተሠባብረው መስራት አይችሉም፡፡ …>> ( ከመድረኩ ተሳታፊ በእንባ የታጀበ ንግግር የተቀነጨበ)
.
…ኢህአዲግ ከፈፀማቸው እጅግ አሰቃቂ ግፎች መካከል በወሎ ሙስሊሞች ላይ የፈፀመው ግፍ በአንድ ጀምበር ተፅፎም ይሁን ተነግሮ አያልቅም፡፡ በርካቶች ሙስሊም በመሆናቸው ብቻ << አሸባሪ>> እየተባሉ ለእስር ፣ ለስደት ፣ ለአካል መጉደል ተዳርገዋል፡፡ በ08/08/2010 ዓ.ም የአብክመ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ፤ ከደሴ ፣ ከኮምቦልቻ ፣ ከደጋን ፣ ከሀርቡ ፣ ከከሚሴ ፣ …. ተወክለው ከመጡ ሙስሊሞች ጋር ፤ በደሴ ከተማ በሀጂ ሁሴን አልአሙዲን ሩቅያ አዳራሽ ስብሰባ አድርገው ነበር፡፡ የዚህ ስብሰባ አላማ የሙስሊሙን ጥያቄ ለመመለስ የሚል ቢሆንም በመድረኩ የተነሱት ጥያቄዎችና የፈሠሠው እንባ ግን አሁንም ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት የሚቻልበትን ሁኔታ አያመላክትም፡፡ << እኔ ዛሬ የተገኘሁት ልንናገር ሳይሆን ፤ የእናንተን በደል ለመስማት ነው፡፡>> በማለት ስብሰባውን የጀመሩት አቶ ገዱ ፤ ከየአቅጣጫው የተሠባሠበው የወሎ ህዝበ ሙስሊም ፤ በምሬትና በእንባ ታጅቦ ብሶቱንና በደሉን ሲያፈስ ፤ የአቶ ገዱን ስሜት በከፍተኛ ሁኔታ ሲፈታተናቸው ተስተውሏል፡፡ በመድረኩ ከተነሱ አንኳር እንኳሮቹን እንደሚከተለው አቀርባለሁ ፦
<< መንግስት በሀይማኖታችን ጣልቃ በመግባት ፤ የማይወክሉንን ካድሬዎች በመጅሊስነት በመሠየም ፤ ይህንን በመቃወማችንም መፈጠርን የሚያስጠላ ሰቆቃና ግፍ ተፈፅሞብናል፡፡ >>
<< ከ800 በላይ ከተማውን ሲያለሙ የነበሩ ሙስሊም ባለሀብት ነጋዴዎች ፤ በሀይማኖታቸው ምክንያት በደረሰባቸው በደል ከደሴ ተሠደዋል፡፡ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ከተማዋን ለቀው ለህገ ወጥ ስደትና አድራሻ ለመቀየር ተገደዋል፡፡ >>
<< አሁንም አሸባሪዎች አንሠራሩ እያሉ የማሸማቀቅና የማስፈራሪያ ዛቻ እየፈፀሙብን ያሉት ፤ የመንግሥት ሠዎች ናቸው፡፡ >>
.
<< … በሙስሊም በመሆኔ ብቻ “አሸባሪ” ተብዬ ከፍተኛ ድብደባ ተፈፅሞብኛል፡፡ በገመድ አስረው ሸንተውብኛል፡፡ ጣቶቼ ተሠባብረው መስራት አይችሉም፡፡ >> ( በእንባ ታጅቦ በደሉን የተናገረ ግለሠብ)
<< መንግስት የወከላቸው ፤ ካድሬዎች ሙስሊሙ በወከላቸው የመጅሊስ አመራሮች መተካት አለባቸው፡፡ ይህ ካልሆነ አሁንም ያው ነው፡፡ >>
<< እምነታችን የሚፈቅደውን ሂጃብ በመልበሳችን ” አሸባሪ ተብለን ከታሰርን በኃላ ፤ ልብሳችንን አስወልቀው ገርፈውናል ፣ ተፍተውብናል ፣ በለሊት አስወጥተውም አባረውናል! >> ( ሴት ተሳታፊዎች )
.
የመሳሰሉት በመድረኩ የተነሱ ጥቂቶቹ አንኳር ነጥቦች ሲሆኑ መድረኩ ፤ ከተጠበቀው በላይ ብሶትና ሀዘን እንደጅረት የፈሠሠበት ነበር፡፡ አቶ ገዱ በህዝበ ሙስሊሙ ላይ የተፈፀመውን ግፍ ያለመታከት በአጀንዳቸው ሲመዘግቡ የነበረ ሲሆን ለአንዳንዶቹ ጥያቄዎችም ምላሽ ለመስጠት ሞክረዋል፡፡ መጅሊሱን በተመለከተ ለተጠየቁት << መጅሊሱን እኛ ማውረድ አንችልም፡፡ እራሱን የቻለ ህግና ስርአት አለው፡፡ >> ሲሉ ፤ ተሳታፊዎች በበኩላቸው << እኛ ሳንመርጣቸው ፤ እናንተ የሾማችኃቸውን ሙስሊሙን የማይወክሉ ሹመኞች ልታወርዱ የሚገባው እናንተው ናችሁ፡፡ >> ሲሉ ሞግተዋቸዋል፡፡ << ስም እየጠቀሳችሁ አስተያየት የሠጣችሁና የተፈፀመባችሁን ግፍ ያጋለጣችሁ ፤ ምንም እንደማይደርስባችሁ ቃል እገባለሁ!!! ለጥያቄዎቻችሁም ጊዜ ሠጥቸን መፍትሄ እንፈልጋለን፡፡ …. ከአሁን በፊት የተፈፀመባችሁ ግፍ ዳግመኛ አይከሰትም፡፡ በስደት ያሉትም ሆነ ከተማዋን ጥለው የሄዱትን ሙስሊም ነጋዴዎች ተባብረን መልሰን ከተማችንን እናልማ! ..>> የሚል አስተያየት የሠጡት አቶ ገዱ ፤ መድረኩ ከጠበቁት በላይ ጠንካራና የአንድ ጀምበር ጉዳይ ብቻ አለመሆኑ ፤ ስብሰባውን በይደር ለመቋጨት አስገድዷቸዋል፡፡ የክልሉ የመጅሊስ ተወካዮች በበኩላቸው ፤ ያለእኛ እውቅና ህዝበ ሙስሊሙን በመሠብሰባቸው አቶ ገዱ ላይ ተቃውሞ እንዳቀረቡ ለማረጋገጥ ተችሏል ፡፡ የወሎ ህዝበ ሙስሊሞችም የደረሠባቸውን የበደል ፍላሎትና የተዳፈነውን ረመጥ የነካካባቸውን ስብሰባ ታድመው ተመልሠዋል፡፡ ዛሬ በደረሰኝ መረጃ መሠረት ደግሞ በመድረኩ ስማቸው ተጠርቶ ፤ የፈፀሙት ግፍ የተነገረባቸው የፖሊስ አዛዦችና ሹማምንቶች ፤ ተናጋሪዎችን እያሳደዱ እንደሆነ ለማወቅ ችያለሁ፡፡
ጀዛ ከላህ ኸይር!