በተመድ የሰብዓዊ መብት ባለስልጣናትና በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጠበቆች እና አባገዳ ምክር ቤት ጋር የነበረው ስብሰባ በወያኔ ጫና ተቋረጠ

(ምንሊክ ሳልሳዊ)

በተመድ የሰብዓዊ መብት ድርጅትና በአባገዳ ምክር ቤት መካከል የተጀመረ ስብሰባ እንዲሁም የዚሁ አካል የሆነው በሰብዓዊ መብት ጠበቆችና በኢትዮጵያውያን ጠበቆች መካከል የተጀመረ ስብሰባ በወያኔ ግፊት ተቋረጠ። መረጃዎች እንደሚያሳዩት የ አባገዳ ምክር ቤት መሪ የሆኑ አባገዳ በየነ ሰንበቶ እንዲሁም የቢሾፍቱ ከተማ ባለስልጣናትና የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የተሳተፉበት እና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ባለስልጣናት ጋር ለመነጋገር የተዘጋጀው ስብሰባ በ አባገዳ በየነ ሰንበቶ ላይ የወያኔ ባለስልጣናት የእሬቻን ጭፍጨፋ አስመልክቶ ጫና ለማድረግ ሲሞክሩ በተፈጠረው አለመግባባት ስብሰባው እንዲቆም ተደርጓል። ወያኔዎች እነሱ በሚፈልጉት መንገድ እንዲነገርላቸውና መንግስት ተሃድሶ ላይ ነው ተብሎ እንዲሰበክላቸው ቢፈልጉም አልተሳካላቸውም።

እንዲሁም ከሰብዓዊ መብት ድርጅቱ ጋር የተቀናጁ የሉኡካን ቡድን ኣባል የሆኑት የሰብዓዊ መብት ጠበቆች በሽብር ክስ ለተከሰሱ የፖለቲካ አስረኞች ተከሳሾች ጥብቅና የቆሙትን ጠበቃ ሚኪያስ ቡልቻና ጠበቃ አብዱልጃብር ገመዳ እያነጋገሩ ባሉበት ወቅት ላይ ለተባበሩት መንግስታት ስታፎች ከወያኔ ባለስልጣናት ስልክ ተደውሎ በ አስቸኳይ ስብሰባው እንዲቋረጥ መደረጉን መረጃዎች ጠቁመዋል። የቢሾፍቱ ባለስልጣናትም ከበላይ የመጣ ትእዛዝ ነው በማለት ስብሰባውን መበተናቸው ታውቋል። ይህ ስብሰባ እንዲደረግ የመንግስት ባለስልጣናት ፈቃደኞች አለመሆናቸውን ስለነገሩን ስብሰባውን አቁመናል ሲሉ የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ጠበቃ ተናግረዋል።