እነርሱና እኛ – የኦሮሞ ማህበረሰብን በተመለከተ #ግርማ_ካ

ከጥቂት አመታት በፊት “የኦሮሞ አክራሪዎችና እኛ” በሚል አንድ ጽሁፍ አቅርቤ ነበር። በዚህ ጽሁፍ ላይ የተቀመጡ አንዳንድ ነጥቦችን ወስጄ፣ የአቶ ለማ መገርሳ ቡድን አይሎ ከመውጣቱ በፊት የነበሩ፣ የነርሱን ጠባብ ፍላጎት ለማርካት ለህወሃት የከፋፍለህ ግዛ መሳሪያና ኮርቻዎች፣ የኦነግ/ኦህዴድ ሰዎች፣ ሲያራምዱት በነበረው የኦሮሞዉን ማሀበረሰብ በፊደል፣ በስነልቦና፣ በርዮት አለም ከሌላው ማህበረሰብ የመነጠል እንቅስቃሴ፣ ከማንም በላይ የኦሮሞ ማህበረሰብን ራሱ እንደጎዳ ለማሳየት እሞክራለሁ፡

እኛ የኢትዮጵያዊ ግንድ የሆነው የኦሮሞ አካልም በመሆናችን፣ ኦሮሞነትም ኢትዮጵያዊነት በመሆኑ፣ የነዚህ ሰዎች ፖለቲካ ኦሮሞ ላይ ምን ያህል አሉታዊ ጫና እንዳሳደረ በማሳየት፣ ማህበረሰቡን በተጨባጭ የሚጠቅሙ ነጥቦችን ለማስቀመጥ አሞክራለሁ።

፩ – እነርሱ ኦሮሞው ከአማርኛ ጋር ተጣልቶ፣ የመሻሻል እድሉ ጠቦ እንዲኖር ነው የሚፈልጉት።ትልቁ ቀጣሪ በሆነው በፌዴራል መንግስት፣ በአማራ፣ በደቡብ፣ በቤኔሻንጉል፣በጋምቤላ ክልሎች፣ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተሞች … ሥራ እንዳያገኝ። እኛ ኦሮሞው የአገሪቷን ዋና ቋንቋ አማርኛ ተምሮ፣ መጻፍና ማንበብ ችሎ በሁሉም የአገሪቷ ክፍል ያለ ምንም የቋንቋ ተጽኖ እንዲሰራ ነው የምንፈልገው።

፪. እነርሱ አፋን ኦሮሞ እንደማንነት መገለጫ ነው የሚያዩት። ከዚህም የተነሳ አማርኛ በመናገራቸው ኦሮሞነታቸውን ያጡ ይመስላቸዋል። እኛ ቋንቋ የማንነት መገለጫ ሳይሆን መግባቢያ ነው ባዮች ነን። አሁን አላውቅም እንጅ፣ በፊት ግን በሐረር ያሉ ኦሮምኛም፣ አማርኛም አንዳንዶቹ አደርኛና ሶማሌኛም ይናገሩ ነበር። በወልቃይት ትግሪኛ፣ አማርኛ አንዳንድ ቦታም ዐረብኛ ይናገራሉ። ቋንቋ የማንነት መገለጫ ተደረጎ መወሰድ ሲጀመር ግን፣ ትግሪኛ የተናገረ ትግሬ ነው ሲባል ግን ችግር ተፈጠረ።

፫. እነርሱ ልጆቻቸውን ደህና ት/ቤት እያስተማሩ ነው፣ ለርካሽና የኋላ ቀር የፖለቲካ አይዲዮሎጂያቸው ብለው፣ አማርኛ እንዲጠላ በማድረግ በድሃው ኦሮሞ ልጅ ሕይወት የሚጫወቱት ። እኛ ልጆቻችን ጥሩ የወደፊት እድል እንዲገጥማቸው እንደምንፈልገው የኦሮሞም ልጅ ብሩህ ሕይወት እንዲኖረው ነው የምንፈልገው። ስራ አጥቶ እንዲጎሳቆል አንፈልግም።

፬. እነርሱ በዘረኛና ጠባብ ፖሊሲዎቻቸው በኦሮሞው ማኅበረሰብና በሌላው መካከል መቃቃርና ልዩነት እንዲፈጠር ይሰራሉ። ከዚህ የተነሳ ኦሮሞው በብዛት በሚኖርባቸው ከአዲስ አበባ ራቅ ባሉ አክባቢዎች የንግድ፣ የቱሪዝም የመሳሰሉ እንቅስቅሴዎች በስፋት ሊስፋፋ አልቻለም። እስቲ አስቡት አሁን ማንነው የዓኖሌ ሐውልት ያለበት አካባቢ ሳይፈራ የሚሄደው? ሕዝቡ ደግና እንግዳ ተቀባይ ሆኖ ሳለ፣ በሌላው አይምሮ ውስጥ ግን ከኦሮሞው ጋር በጭራሽ የማይገናኝ አስተሳሰብ እንዲገባ ተደርጓል። ሌላው እንዲፈራ ከመደረጉ የተነሳ፣ እንደ አዋሳ፣ ባህር ዳር ያሉ፣ አሶሳ ሳትቀር ፣ ሲሻሻሉ እንደ ነቅምቴ፣ መቱ … ያሉ ግን ወድቀዋል። እኛ ዘረኞች የዘረገቱን የመፈራራት ግንብ ፈርሶ ኦሮሞው በባህሉ እንግዳ ተቀባይ ሌላው የሚያቅፍና እንደ እራሱ አድርጎ የሚቀበል (በጉዲፍቻ ባህል እንዳየነው) መሆኑን፣ ኦሮሞው ሌላው ጠላቱ ሳይሆን፣ ከሌላው ጋር የተዋለደና የተዛመደ መሆኑን እያስረዳን፣ ሁሉም ዜጎች ወደ ባህር ዳርና ወደ አዋሳ ሲሄዱ ነጻነት እንደሚሰማቸው ወደ ሁሉም የኦሮሚያ ግዛቶች ለመሄድም ነጻነት እንዲሰማቸው ለማድረግ ነው የምንሰራው። እነ ነቀምት፣ እነ አሰላ እነ መቱ በንግድ በቱሪዝም እንዲያድጉ፣ እንዲሻሻሉ ነው የምንፈልገው።

፭. እነርሱ አፋን ኦሮሞ በኦሮሚያ ውስጥ ብቻ ተወስኖ፣ ኦሮሞው ከሌላው ጋር እንዳይገባባና እንዳይነጋገር፣ እንዲለያይ ነው የሚሰሩት። እኛ አፋን ኦሮሞ ከኦሮሚያም አልፎም በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ እንዲነገር፣ ከኦሮሚያ ውጭ ባሉ ትምህርት ቤቶች እንደ ሰብጀክት እንዲሰጥ ነው የምንፈልገው። ( በቅርቡ እኔን ጨምሮ በርካታ ምሁራን በአማራ ክልል አፋን ኦሮሞ በግእዝ እንዲሰጥ የሚጠይቅ ጥናታዊ ሰነድ ለተከበሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አቅርበን ነበር) ከዚህም የተነሳ ለምሳሌ ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች አማርኛን በደንብ አውቀው አዲስ አበባ ሲመጡ በነጻነት ከከተሜው ጋር እንዲግባቡ፣ የአዲስ አበባ ልጆችም ወደ ገጠር ሲሄዱ በአፋን ኦሮሞ ከገበሬው ጋር እንዲግባቡ ነው የምንፈልገው።

፮. እነርሱ ኦሮሞውን በጠባብነት ጆንያ አሳንሰው ነው የሚያዩት። መገንጠልን፣ ልዩነትን፣ ጥላቻን፣ ቁርሾች ነው የሚያስተምሩት። እኛ የኦሮሞውን ግንድነት፣ አሁን ያለችዋን ኢትዮጵያ በማቅናት ዙሪያ የኦሮሞውን ጉልህ ሚና ነው የምንናገረው።

፯. እነርሱ አገር አስገንጣይ፣ የውጭ ወራሪዎች ተባባሪዎችን፣ ዘረኞች ነው እንደ ሞዴላቸው የሚያዩት፤ እንደ ዋቆ ጉቶ ያሉትን። እኛ እንደ ባልቻ አባ ነፍሶ፣ አብዲሳ አጋ፣ ጀነራል ጃጋማ ኬሎ፣ አባመላ ፊታወራሪ ሃብቴ ዲንግዴን፣ ጀነራል ደምሴ ብልቱ፣ አቡነ ጴጥሮስ (አባ መገርሳ) … ያሉትን፣ አገር ያቀኑ የሕዝብ ኩራት የሆኑ የኦሮሞ ጀግኖችን ነው የምንዘክረው።

፰. እነርሱ የኢትዮጵያው ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ሃብትና ቅርስ የሆነው የግዕዝ ፊደልን በመጸየፍ፣ ፈረንጆችን እንደ ጌታ የማየት የባሪያነትና የበታችነት መንፈስ ስለተናወጣቸው፣ ከአፋን ኦሮሞ ሆነ ከኦሮምሞ ጋር ምንም ያልተገናኘ የላቲን ፊደል በሕዝቡ ላይ የዘረጉ ናቸው። እኛ የቀደምት የኦሮሞ ልሂቃን፣ እንደ አናሲሞስ ነሲቡ ያሉ፣ የተጠቀሙበትን የኦሮሞውም ኩራት የሆነውን ኢትዮጵያዊ ፊደል እንጠቅም ባይ ነን።

፱. እነርሱ ኦሮሞውን ከሌላው ማህበረሰብ በማጣላትና በመነጠል ለውጥ ይመጣል ባዮች ናቸው። እኛ ኦሮሞው ትግሉን ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወንድሙ ጋር በማቀናጀት በኢትዮዮጵያዊነት ጥላ ስር ቢያደርግ፣ ከሌላው ጋር እጅ ለእጅ ቢያያዝ ተዓምር መስራት ይችላል ባዮች ነን።

፲. እነርሱ ኦሮመነትን ከኢትዮጵያዊነት ያስቀድማሉ። የኦሮሞ ብሄረተኞች ናቸው። የኢትዮጵያዊነት ማንነት የለም ይላሉ። እኛ የተከበሩ ዶር አብይ አህመድ “የኦሮሞ ብሄረተኝኘት ትልቁን ኦሮሞ ማሳነስ ነው” እንዳሉት የኢትዮጵያዊ ማንነት የካዳ ኦሮሞነት ከኢትዮጵያዊነት ጋር የተጣምደውን የኢትዮጵያ ግንድ የሆነው የኦሮሞ ማህበረሰብ መስደብ ነው እንላለን። ኦሮሞ ኢትዮጵያ ብሎ አገር ሲያቀና፣ ታሪክ ሲሰራ ነው የምናወቀው እንላለን።