ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ጊዜያዊ አዋጁን ያንሱልን (ይፍሩ ኃይሉ)

ከይፍሩ ኃይሉ

ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ

በመጀመሪያ ለርስዎም ሆነ ለተቀመጡበት ሥልጣን ወንበር ከፍ ያለ አክብሮት ስለአለኝ የአክብሮት ሰላምታዬንና መልካም ምኞቴን በታላቅ ትሕትና አስቀድማለሁ። ቀጥዬም ይህቺን መልዕክት ለመጻፍ ወደ አነሳሳኝ በቀጥታ እገባለሁ።

ለሃያ ሰባት ዓመታት ታፍኖና ተጨቁኖ፤ ያለፍርድ በወያኔ ወህኒ ቤቶች ታጉሮ፤ በግፍ እየተሰቃየ ሲማቅቅ የኖረዉ፤ ያልታደለዉም በአጋዚ አልሞ ተኳሾሽ፤ አዋቂ ሳይል ሕጻኑ፤ ሽማግሌ ሳይል ባልቴት በጥይት እየተደበደበ ሕይወቱ ባጭር ሲቀጭ፤ መከራና ስቃዩም የበዛበት ሕይወቱን ለማትረፍ ሲል፤ ተወልዶ ያደገባትን እናት አገሩን ለቆ፤ ድንበር ጥሶ፤ ኬላ ሲያቁርጥ፤ በዘንዶና በጊንጥ፤በውባና በንዳድ በሽታ እየተለከፈ፤በየዱሩና በየበረሃው የትም ወድቆ ሲቀር፤ ከዚያም የተረፈው፤ በቀን የጅቢራና የጥንብ አንሣ አሞራ ምሳ ሆኖ ሲቀር፤ የተረፈዉም የአንበሳና የጅብ እራት ሆኖ የቀረዉን እግዚአብሔርና ታሪክ ይመዝግቡት እንጂ በዚች አጭር ደብዳቤ ለመግለጽ አልቃጣም። ከዚህ ሁሉ ስቃይ ተርፎ እግሩ እስከ ቀይ ባሕር ያደረስው፤ወይም ከምድረ ሱዳን የጣለው፤ ስፍርር ቁጥር የሌለው ወግናችን ግማሹ በሱዳን በርሃ ዉስጥ ሲያልቅ፤ ግማሹም በማይችለው ዋና ቀይ ባሕርን ለመማቋረጥ ሲሞክር የአዞና የአሰናባሪ ቀለብ ሆኗል። እጅግ በጣም የሚያሳዝነው ይህ ግራ የገባው ወግናችን፤ “በረሃ አቋርጬ፤ ባሕር ሰንጥቄ ደረቅ መሬት እረገጥሁ” ብሎ የተስፋ ጭላንጭል ለማየት ሲሞክር፤ የዕለት ጉርሱን ለማግኘት በየሰዉ ቤት ተቀጥሮ ሲሠራ የሚደርስበት የቁም ስቃይ በቃላት ሊገልጽ አይቻልም።

በሌላ አቅጣጫ የሚገጥመዉን የቁም ስቃይ ብቻ ሳይሆን፤ የቻድንና የሊቢያን በረሃ ሲያቁርጥ በሽፍታና በወንበዴ እየተያዘ የክርስትና ሃይማንቱን እንዲክድና የሌላውን እንዲቀበል ሲገደድ “ሃይማኖቴ ወይም ሞት” እያለ እንደ በግ ሲታረድ፤ ወይም ሰምተዋል ወም እንድኛው በዩ ቱበ(YOU TUBE) አይተዉታል ብዬ እገምታለሁ።ከዚህ በላይ እነዚሁ ኢትዮጵያዉያን ወገኖቻችን(ኤርትራትራዉያንን ወንድሞቻንና እህቶቻችን ጨምሮ) በሕይወት እያሉ፤ዓይናቸው እየተቁለጨለጨ፤ ቆዳቸው እየተገፈፈ፤ኩላሊትና ልባቸው፤ዓይንና ሳምባቸው፤ ሌላዉን በሕይወት ለማኖር የሚያስችል የሰዉነት ክፍላቸው፤ እየተመረተ ለንግድ ሲቀርብ አይትዉት ይሆን?? ወይስ ሊኩን ልላክለዎትና እርሰዎም ተመልከተው እንንደኔው የሦስት ቀን በሽታ ይሸምቱ?

ይህ በዚህ እዳለ በአገር ቤትም፤ መከራና ስቃዩ ከዚህ ይከፋ እንጂ ያለነሰ በመሆኑ፤መሬቱ በወያኔ ተወስዶበት፤አርሶ ከሚበላበት የተፈናቀለዉ፤የወልቃይት ጠገዴና የቤኒሻጉል፤ጉምዝ፤የራያና የአዘቦ ሕዝብ ተወልዶ የአደገበትን የአያት የቅድመ አያቱን መሬት በወያኔ ባለሃብቶች ተነጥቆ በራሱ ንብረት ላይ የዘራፊዎቹ ዘበኛና አትክልተኛ፤ ቆፋሪና ኩሊ ሆኖ ላቡን እያንጠፈጠ ይገኛል። አንዳንዱም ባለወኔ እርስቴን፤አለቅም፤በማንነቴንም አልደራደርም፤ ያለዉ ጀግና፤ ባለዉ አቅም በጁ ያለዉን መሣሪያ አንስቶ፤ጨቋኞቹን ና ዘራፊዎቹን ፊት ለፊት ተጋፍጦ በመረጡት መንገድና በሚገባቸዉ ቋንቋ እያረገፋቸውና እሱም ከፍተኛ መስዋዕት በመክፈል ላይ ነዉ። በዚህ ላይ እመለስብታለሁ።

ፍርድ በተጓደለባትና አድለዎ በበዛባት ኢትዮጵያ፤ስንቱ ወጣት ያለች የሌችዉን አንጡራ ሃብቱን አፍሶ፤የወጣትነት አፍላ ዘመን ፤”ተምሬ ነገ የተሻለ ሕይወት መምራት እችላለሁ” በሚል ተስፋ፤በአገሪቷ በሚገኙት ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች

በተለያየ የሙያ ልምድ ሰልጥኖ፤ ተመርቆ፤ ተስፋ ወደ አደረገው የሥራ መስክ ለመሰማራት ሲሞክር፤ እንኳንስ በአንድ በሰለጠነበት ሙያ ተቀጥሮ ለመሥራት ይቅርና፤ በኩሊነት እንኳ የሚቀጥረው ሲያጣ ባንድ ቀን ዠንበር ለተፈለፈሉ ቱጃሮች ተቅጥሮ ለመሥራት ሲሞክርም “የወያኔ ፓርቲ አባል ካልሆንክ ሲያምርህ ይቅር” ይባላል። ታዲያ ይህ ኑሮ ያንገፈገፈዉ ሥራ ፈት ወጣት፤መብቱን

ለማስከበር፤ በሰላማዊ መንገድ ‘የሥራ ያለህ! የፍትህ ያለህ!’ እያለ ጉሮሮው እስከሚሰነጠቅ መጮህ ሲጀምር ያገኘዉ መልስ አሁንም በአጋዚ አልሞ ተኳሾች የጥይት እሩምታ ይወርድበታል። ሞትን አይፈሬዉ ወጣት ትዉልድ፤ ጥይት እንደ ዝናብ እወረደበት፤ በሚችለዉ መንገድ ሁሉ ድምጹ እንዲስማለትና ለጥያቄዉ መልስ ለማግኘት፤ ያለ የሌለ አቅሙን እየተጠቀመ፤ በአንድነት በመተባበር ቆሞ፤መንገድ መዝጋት፤የዛራፊዎችን ንብረት ዒላማ ዉስጥ አስግብቶ የወያኔን መንግሥት ሳይወድ በግድ እንዲያዳምጥ አስገደደዉ። ወያኔም ሃላፊነቱን ወደ ሌላ ለማስተላለፍ ሲሞክር የፈርደባቸዉን፤ለይስሙላ ተቀምጠዉ የነበሩትን አፈቀላጤዉን፤ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ከሥልጣናቸው እንዲለቁ አደረገ። ግን አልሠራም። አቶ ኃይለማርያም የችግሩ መንሰዔ አልነበሩምና። ግን ወያኔም ሳያውቀው፤ እሳቸዉም ሳያስቡት፤ በኢትዮጵያ ትልቁ እስረኛ የነበሩት አቶ ኃይሀ ማርያም በግርግር ነጻ ወጡ።

በዚህ ቀውጢና አጣብቂኝ ወቅት ነዉ የሦስት ድንቅ ኢትዮጵያዉያን ስምና ሥዕል(ፍቶ ግራፍ) በየቴሌቪኑ መስኮትና በየ ሶሻል ሜዳያው ፤” ለማ መገርሳ፤ደጉ አንዳርጋቸው፤ዶከትር አቢይ አህመድ፡የተባሉት ግለሰቦች ስም መስማት የጀመርነዉ፡፤ የሚገርመዉ በረቀቀና በሰለጠነ መንገድ እነዚህ ግለሶብች የወጣቱንም፤ ሆነ በጠቅላላ የኢትዮጵያን ሕዝብ ቀልብ ለመሳብ ቻሉ። በይበልጥ ግን የወያኔ መንግሥት ባልጠበቀዉ፤ ባላሰበውና ባልጠረጠርው መንግድ፤እነዚ ከሁለት ታላቅ ሕዝብ አብራክ የተገኙ የአማራና የኦሮሞ ምርጥ ልጆች፤በወያኔ ካምፕ ዉስጥ ተጠንሦ፤በሁለቱ ብሔሮች መሃል ሲሰራጭ የነበረዉ የጥላቻን መርዝ በአንድ ጊዜ አብረሰው(ነውትራሊዝ)፤አክሽፈዉ። ልዩነታቸዉን አቻችለዉ፤”አንድ ነን!፡አንለያይም! ብለዉ የጋራ ጠላታቸዉን በአንድ ላይ ሊቋቋሙት መወሰናቸዉን የጠላት ጎራ ሲሰማ፤ የቆመባት መሬት እየከዳችዉ መሆኑ ቁልጭ ብሎ ታየዉ።በምሽጉ ነፍስ ዉጪ ፤ ነፍስ ግቢ ሆነ።

በአቶ ኃለማርያም ደሳለኝ ባልታሰበና ባልተጠበቀ መንገድ ከሥልጣን መውረድ የፈጠረዉን የጠቅላይ ምኒስትርነት ክፍት ቦታ ለመሙላት፤ በዚህም በዚያም ሩጫዉ ተጣደፈ። በተለይም ወያኔን ያስጭነቀው፤ የአቶ ለማ መገርሳና የአቶ ደጉ አጋርጋቸዉ ወደ ከፍተኛ ሥልጣን መቃረብ ስለነብረ፤ ወያኔ በተቻለዉ መጠን እነዚህን ሁለት ገለሰቦች ከጫወታዉ ዉጪ ለማድረግ የተቻለዉን ሁሉ ቢያደርግም፤ አሁን ሳይወድ በግድ “ይህን ዶክተር አቢይ የተባለዉንስ ምን ማድረግ ይሻላል? የሚለዉ ጥያቄ አሁንም እንቅልፍና ጤና ነሳዉ።የተቻለዉን ሁሉ ሞከረ፤ግን አለትሳካም። ምርጫዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆነና ክቡርነትዎን በክፍተኛ ድምጽ መርጦ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሆኑ አደረገ ።

ሥልጣኑን በተረከቡበት ዕለት ቢትዮጵያ ፓርላማ ዉስጥ ቆመዉ ያደረጉት ታሪካዊ ንግግር ሁሉንም አስደመመ።ከሃያ ሰባት ዓመታት በኋላ፤ በአደባባይ ቆሞ፤”ኢትዮጵያ ሃገሬን እግዚአብሔር ይጠብቅ “የሚል መሪ አገኘች። የኢትዮጵያ ሕዝብ ደስታ ልክ ሊግኝለት አልቻለም ነበር። የተስፋ ጭላንጭል፤ አብሮ ለመኖርና ዛሬ ለፉክክር፤ነገ ለዉድድር፤ለመቅርብ የሚያስችል ተስፋና የሚያሳይ ጮራ ፈነጠቀ” አለ።

የኢትዮጵያም ሕዝብ ተስፋ ሆነ የዓለም ታዛቢዎች አስተያየት፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በሰጡት ተስፋና በገቡለት ቃል እጅግ በጣም ተጽናና። በፈነጠቁለት ተስፋ አሁንም በመደነቅ ላይ እያለ፤ ክቡርነትዎ፤የሃገረዎን ሕዝብ በየአካባቢው እየተዘዋወሩ ማነጋገርና የሕዝቡን የልብ ትርታና ስሜት ለማግኘት፤ከወዲያ ወዲህ መሯሯጡን ተያያዙት። በመጀመሪያም ወደ ጂጂጋ አቅንተዉ ያገሬውን ሕዝብ ሳያስበዉ በደስታ አስፈንደቁት። ሕዝቡም አከበረዎት፤ ወደደዎት። ሳይዉሉም ሳያድሩም ይህን ታሪካዊ ጉዞ በአምቦ ከትማ ደገሙት። ከማን አንሼ ይመስል፤ የአምቦም ሕዝብ ደስታ እንደ ጂጂጋው ልክ አልነበረዉም። የሚቀጥለው አጀንዳቸዉ ምን ይሆን ብለን ሳንጨርስ ወደ መቀሌ ትግራይ ገሰገሱ።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር! ለርሰዎ ያለኝ አክብሮት እንዳለ ሆኖ በትግራይ ጉብኝተዎ ላይ፤ በመቀሌ ከተማ ለትግራይ ሕዝብ ባደረጉት ንግግር ላይና በንግግርዎ መጨረሻ ላይ የሥነስረኣት አምፈጻጸም ቅሬታዬን ስገልጽልዎ አሁንም በአክብሮት ነው።

እርሰዎን የመሰለ አዲስ መሪ ፤በአዲስ ጉልበት አገሩን የሚያገለግል፤ ችግራችንን የሚፈታ፤ለሰላምና ለፍትሕ ለዲሞክራሲና ለመብታችን የሚቆም መሪ አገኘን ብለን፤ ዳስ ጥለን ፤ድንኳን ተክለን፤ ቤት ሙሉ ደግሰን አራሞዉን እየደለቅን፤ ጨፍረን ሳንጨርስ፤ ክቡርነተዎ በመቀሌ ላይ የጭቃ ጅርራፍዎን ማጮህ ሲጀምሩ በጣም ደነገጥን፤ በጣምም ከፋን።

በበኩሌ ቅሬታዬ ትግራይ ሄደዉ ለምን በትግርኛ ተናገሩ ብዬ አይደለም። እንኳንስ ችሎታዉ ኖረዎት፤ በሄዱበት ሁሉ የአካባቢዉን ሕዝብ በቀላሉ በሚገባው ቋንቋ ማናገር ቢችሉ እንዴት መልካም ሆነ ነበር! በዚያ ግሩም በሆነ የቋንቋና የአነጋገር ችሎታዎ ትግርኛውን ሲያቀላጥፉት ሠሰማ ምን ያህል እንደተድንቅሁና ምን ያህል እንደቀናሁ ብነግርዎ ይደነቃሉ።

የኔ ቅሬታ ለምን የትግራይን ሕዝብ “ወርቅ “ ብለዉ ጠሩት ብዬ አይደለም። እርግጥ ነዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ በጠቅላላ፤ የትግራይንም ሕዝብ ጨምሮ ሁሉም ወርቅ ነው። በዚህ ላይ በጭራሽ አንከራከርም። የኔ ቅሬታ፤ የሕወሓት፤ ትግራይን ተጋዳዮች ጀግኖች እያሉ ሲያቆላምጡ በመስማቴ በጣም፤ አዝኛለሁ። ገርሞኛልም።

የወያኔ ጀግንነት ኤርትራን አስግንጥሎ፤ እናት አገረዎን ኢትዮጵያን ወደብ አልባ ስለአደረገ ነው? የወያኔ ጀግንነት፤ከተገንጣይ ሻብያ ጋር አብሮ የኢትዮጵያን ሠራዊት ስለወጋና አዳክሞ ስለበተነ ነዉ።?

የወያኔ ጀግንነት በሻቢያ የጦር መኮንኖች እየተመራ ወደ መሃል አገርገብቶ፤ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ፤ የኢትዮጵያን አንጡራ ሁብትና ዉርስና ቅርስ እያስዘረፈ ፤እሱም እየዘረፈ ወደ ኤርትራና ወደ ትግራይ ስለአሸሸና አሁንም ከሻቢያ ወራሪ ጦር ጋር ትብብሩን አጠናክሮ ከአዲስ አበባና ከሌሎች የክፍለ ሃገር ከተሞች፤ ጀነሬተር ሳይቀረው ስለዘረፈና ስለአዘረፈ ነዉ።

የወያኔ ጀግንነት፤ የትዮጵያን ሕዝብ በዘር፤ በቋንቋና በሃይማኖት እየከፋፈለ እርስ በርሱ እሣትና ጭድ አድርጎ ለማፋጀት ስለጠነሠው መርዝ ነዉ?

ምነዋ ዶክተር አብይ! በጉራ ፈርዳ፤ በቤሻጉል፤ በበደኖና ቡኖ በበደሌ፤ በአማሬሳ፤ በአርሲ፤ በጋምቤላና በተለያዩ ክልል የሰፈረውን የአማራ ተወላጅ “መጤ” ነህና ፈጥነህ አገር ልቀቅ” እየተባለ ከነነፍሱ ገደል ተወርዉሮ ያለቀዉ የአማራዉ ወገነዎ ደም ዛሬም እየጮኸ መሆኑን ዘነጉት እንዴ?

ከ1997 ምርጫ ሽንፈት በኋላ “ድምጼ ተነጠቀ ብሎ፤ ለሰላማዊ ሰልፍ ወጥተው፤ በወያኔ ጥይት ተደብድበው ያለቁት የንጹሓን ኢትዮጵያዉያን ደም የወያኔን ጨምሮ፤ ከወያኔ ጦር ሌላ ማን በሃላፊንት የሚጠየቅ ይመስለዎታል? ወገነዎ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንን ከርሰዎ አንደበታጋዮች ጀግና ሊያስብል ይችላል እንዴ?

በኢሬቻ በዓል ላይ ላለቀዉስ ደም ማን ይሆን የሚጠየቅ ዶክተር አቢይ? ብዙም ሳንርቅ ትላንትናና ዛሬ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የሚፍጸመው ግፍ፤ በሐረር የትረሽነችዋ ነፍሰጡር ሲወጣ ለመስማት በጭራሽ አልተዘጋጀም ነበር። በዚህ አስደንጋጭና አስገራሚ ንግግርዎ በመገረም ላይ እያለ ይባስ ብለው “ በወያኔ የሰማዕታት ሓዉልት ስር የአበባ ጎንጉን ሲያስቀምጡም በመገረም ተመለከተዎት።ትላንት የኢትዮጵያን ሠራዊት፤ ዛሬ ልጆቹን ያላንዳች እርሕራሔ ሲፈጅ ለወደቀው፤ ነፍሰ ገዳይ የሕወሓት ወታደር” ባጭር ታጣቂው ጀግናው የትግራይ ልጅ” እያሉም እጅግ በጣም ሲያሞግሱት፤ ሲያወድሱት ሰማንዎት። ያልተረዱልን ዋናው ቁም ነገር፤ያንን የሕወሓት ሰማዕታት ሓዉልት የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመለከተው፤ አርሲ ላይ አኖሌ በመባል ከቆመዉ ሓዉልት ለይቶ አይደለም።ሁለቱም የማይሽር ቁስል ማስታወሻዎች ናቸው።

በዚህ ብቻም አላቆሙም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፤ “የወልቃይት ጥያቄ፤ የልማት ጥያቄ ስለሆነ የፌደራሉን መንግሥት ጣልቃ ገብነት አያሻዉም፤ ጎንደርና ትግራይ ሊፈቱት የሚቻል ስለሆነ የነዶክተር ደብረጽዮን ጉዳይ ነው።” ብለው አረፉ።የጀግናው የቴዎድሮስ ዘር፤”እትብቴ ተቆርጦ በተቀበረበት፤በወልቃይት ጠገዴ ትግሬ ነህና በትግርኛ ተናገር፤ተብዬ ማንነቴ ሲገፈፍ፤ መብቴን ለማስከበር፤ማነቴን ለማረጋገጥ ለማነሳው ጥያቄ ያገኘህት መልስ፤እጅ እግሬ በሰንሰለት እየተቀፈደደ፤ ወደ ተዘጋጀልኝ ወሕኒ ቤት መወርወር ወይም በወያኔ ጥይት ተደብድቦ መሞት ከሆነ፤ ለጥያቂዬ ትክክለኛው ፍርድን እስከማገኝ ድረስ፤ጩኸቴን አላቆምም” ያለዉን የጎንደርንና የኢትዮጵያን ሕዝብ በጠቅላላ፤ የወልቃይት ጠገዴን ሕዝብ በተለይ እጅግ በጣም አሳዝነዉታል፤አስቆጥተዉታል።ይህ አባባልዎ የራያና አዘቦንና የቤኒሻጉልን ሕዝብንም ዓይን ጓግጧል።

እግረመንገደዎንም፤ በቅርብ ዕርቀት ከጎነዎ ቆሞ፤ በፖሊቲካዉና በዲፕሎሲም እረድፍ፤በይበልጥም ለሃገሩና ለወገኑ በሚያደርገዉ የገንዘብ መዋጮ ርብርቦሽ፤ የሃግሪቷን የገዘብ እጥረት (Hard currency shortage) ለመቅረፍ በብዙ መንገድ ሊረዳ የሚችለዉን ዲያስፖራ ወገነዎን፤ ክብሩንና የማምዛዘን ችሎታዉን ዝቅ አድርገዉ በመመልከትዎ እጅግ አዝኗል።

በዲያስፖራው ያለዉ ወገንዎ እኮ በናት አገሩ ዉስጥ ሰላምና መረጋጋት፤የሕግ የበላይነትና ዲሞክራሲ ቢሰፍኑለት ፤አገሩ ተመልሶ; ፤ ከወገኑ ጎን በእኩልነት ቆሞ፤ለዘመናት ከምዕራቡ ዓለም የቀሰመዉን ዕዉቀቱን ለወገኑ ለማካፈል፤መምህር/ፕሮፌሶር ሆኖ የሚያስተምር፤ ሓኪም /ወጌሻ፤ ቀዶ ጠጋኝ ሆኖ የሚፈዉስ፤ መሓንዲስ/ቀያሽ ህኖ ከተማ የሚያለማ፤ በተለያየ የንግድ ሥራ ተሰማርቶ ሠርቶ የሚያሠራ፤ ስንት እራሱን አገቱ የቻለዉ የሚያኮራ ቆፍጣና ወገን መሰለዎ?

የዲያስፖራዉ ወገነዎ እኮ፤ በማያዉቀዉና ባለመደዉ ቀበሌ ትላንት በእንግድነት ገብቶ፤ ዛሬ የትላንት አሰሪዉን መልሶ አሠሪ፤ሥራ ፈጣሪ ሆኖ፤ በጥሩ ምሳሌንት ስሙን ያስመዘገበ መሆኑን ቢረዱለት ምን ያህል የሚያኮራና የናት ሃገሩን ስም በበጎ እንጂ በመጥፎ የማያስጠራ፤ ሕግ አክባሪና ታታሪ ሕዝብ እንደሆነ ቢያዉቁለት ምን ያህል በተደሰቱ ነበር!

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር! ግን፤ ሊገባን በማይችል መንገድ፤ ዲያስፖራው ስለኢትዮጵያ ያለው ኢንፎርሜሽን ከፌስ ቡክና ከሶሻል ሜዲያ የሰማዉና ያነበበዉን ብቻ የሚያምን ስለሆነ ስለ አገሩ የሚያዉቀው የተዛበና ከዕዉነት የራቀ ነዉ። የወልቃይት ጥያቄ የልማት፤ ጥያቄ ነዉ እንጂ የሌላ አይደለም። ሕዝቡ የሚያነሳዉ ጥያቄ ለምን ትምህርት ቢት፤ የጤና ጣቢያና መንገድ አልተሠራልኝም ነዉ። ሕዝቡ የሚለዉ የምጠጣው ዉሃ አጣሁ ነዉ፡፡ አይገርምም የጣናንና የተከዜን ሕዝብ ዉሃ ሲጠማው!) የሚለዉና ዲያስፖራው አገሩ ተመልሶ ያለንበትን ሁሌታ በትክክል ቢረዳና ከወገኑ ጎን ተሰልፎ አገር በማልማት ብዙ ሊረዳ ይችላል” ብለዉ ነዉ በደፈናዉ የደመደሙት።

የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ በናቱ ቋንቋ እንዳይናገር፤እንዳይዘፍን፤ሃሳቡን እንዳይለዋወጥ በወያኔ ሕግ ተደንግጎበት፤ ሕጉን ቢጥስ አይቀጡ ቅጣት እንድሚቀጣ፤ አልሰሙም ወይም አያዉቁም ይሆናል ለማለት በጣም እቸገራለሁ። እነኮረኔል ደመቀ ዘዉዱና ስንት የወልቃይት ጠገዴ ጎልማሳና መኳንንት፤ ግንባሩን ለጥይት፤እግሩን ለግር ብረት የሰጠባትን የአያት የቅድመ አያቱን አጽመ እርስት ወልቃይት ጠገዴንና ጠለምትን የወያኔ ወራሪ ጦር ወደ ትግራይ ሲጠቀላቅልበት፤ በሞትና በሽረት ላይ ሆኖ ወራሪና ዘራፊ ጠላቱን እየተፋለመ መሆኑን እያወቁ እንዴት “የማንነት ጥያቄ አይደለም” ይሉታል። በወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ላይ የሚዘንበዉ የመድፍና የአዳፍኔ ጥይት እንኳን ለርሰዎ በቅርብ ላሉት ይቅርና እኛንም ዉቂያኖስ ተሻግሮ እያደነቆረን ነዉ። ደግሞሳ ወራሪዉ የወያኔ ጦር ለወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ምን እያለ እንደሚፎክር አልሰሙ ይሆን? እኔ ልንገረዎ ጌታዬ፤” እኛ የመጣነው መሬታችሁን ለመዉሰድና ሚስቶቻችሁን ለመንጠቅ ነው። የሚለውን መፈክራቸዉን ።

የአማራዉን ሴት በጠቅላላ፤ በተለይም ከዚሁ የወልቃይት ጠገዴ ሴቶች ወልደዉ ዘር እንዳተኩ፤ ያለፈቃዳቸዉ እየተገደዱ የሚያመክን መርፌ እንድሚወጉስ አያዉቁ ይሆን? እንግዲያዉስ ዕዉነቱ፤ ይህ ነዉ። በሚቀጥለዉ የክልል ጉብኝትዎ ጎንደርንም ይጎበኛሉ ብዬ አምናለሁና፤ እኔ ዛሬ በሞላ ጎደል ባጭሩ የዘረዘርኩትን ከሕዝቡ ከራሱ አንደበት እንደሚሰሙት አልጠራጠርም።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር! በመቀሌ ከተማ ባደረጉት ንግግረዎ ላይ በቀላሉ ሊታለፉ የማይቻሉ ስሕተቶች ተሠርተዋል። የሕዝብዎን አክብሮትና ለርስዎ ያለዉን ከፍ ያለ ፍቅርና፤ በርሰዎ ላይ ያለዉን ዕምነት እንደተጠበቀ እንዲቆይ የሚፈልጉ ከሆነ፤ ሳይዉሉና ሳያድሩ፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በጠቅላላ፤ በተለይም ለአማራዉና ለጎንደር ሕዝብ በበለጠ ትኩረት ለወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ፤ ቀጥሎም፤ ሽንጡን ገትሮ ከጎንዎ ቆሞ በማንኛውም ረገድ በሚችለዉ ሁሉ ሊረዳዎ የተዘጋጀዉን የኢትዮጵያን ዲያስፖራ፤ የተብራራና ግልጽና የተስተካከለ ይቅርታ መጠየቅ አለበዎት ብዬ ስለአመንኩ ይህቺን አጭር ደብዳቤ በድፍረት ሳይሆን ከፍ ባለ አክብሮት ላእቀርብለዎ ተገድጃለሁ።

የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር! ከግዚአብሔርና ከወገንዎ ከትዮጵያ ሕዝብ የተቀበሉት ሃላፊነትና አደራ ቀላል እንዳልሆነ እረዳለሁ። ኢትዮጵያ የምትባለዋን ሃገርና ኢትዮጵያዊ የሚለዉን ቃል ከምድር ገጽ ጨርሶ ለማጥፋት ምሎና ተገዝቶ፤ ቆርጦ የመጣው አገር በቀል ጠላት፤ እንደኛዉ ኢትዮጵያዊ የሚመስል፤ቁንቋችንን፤የሚናገር፤ባሕልና ልማዳችንን የሚያዉቅ፤በይበልጥም የአገራችንን ጋራና ሸንተረሩን፤ወንዝና ሸለቆዉን፤ ዉድማዉንና ጫካዉን መዉጭና መግቢያችንን የሚያውቅ መሰሪ ጠላት በመሆኑ፤ ለዘመናት ተስማምቶና ተፋቅሮ፤ተባብሮና ተዛዝኖ የኖረዉን ሕዝብ፤በዘር፤በቋንቋ፤በሃይማኖት ከፋፍሎ’ በመሃላችን ጥላቻንና አለመተማመን ዘርቶ፤ እኛን እያናቆረ፤ለሃያ ሰባት ዓመታት የኢትዮጵያን ሕዝብ በተናጠል እያሰረ፤የተረፈውንም ጨርቁን ጠቅልሎ አገር ጥሎ እንዲሰደድ አደረገዉ።

የኢትዮጵያን ሕዝብ ሃብት እየዘረፈ ወደራሱ ካዝና ከተተዉ።በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ከዓለም ባንክና ከሌሎች ለጋስ አገሮችና በጎ አድራጎት ድርትጅቶች ለምኖ የቃረመውን ኢሮና ዶላር አሁንም እራሱን አበለጸገበት። ልጆቹን በአውሮፓና በአሜሪካ፤እንደዚሁም በሩቅ ምሥራቅ፤ ኮሌጆችና ዩንቨርሲቲዎች አስተማረበት። በአዉሮፓና በአሜሪካ ፎቅና ቪላ ሠራበት። ባለሆቴልና ባለሞቴል ባለቤት ሆነበት። ይህ ወራሪ ጠላት በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላርስና ፓዉንድ በዓለም ዙሪያ ባሉ Off Shore Banks አከማቸ። ስለዚህም የኢትዮጵያ ሕዝብ ዛሬ መሪ ነኝ የሚል ማንንም ለማመን ቢቸገር አይፍረዱበት።

የወረሱት መንግሥት ባላመተማመንና በሙስና የተጨማለቀ፤የፖሊቲካው ሥረዓት ዉጥንቅጡ የወጣ፤ዲሞክራሲና የሕግ የበላይነት የሌለበት፤ ፍትሕ የተጓደለበት፤ አድለዎና ወገንታዊንት የተሰራፋበት ስለሆነ፤ከፊተዎ ተደቅኖ የሚጠብቅዎ የቤት ሥራ ከዝቋላ ተራራ በላይ ነዉ።በተለይም ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በሥልጣን ላይ ተሰራፍተው ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ በሃገርና በሕዝብ ሲቀልዱና እጃቸዉ በንጽሓን ደምና በሌብነት የተጭማለቀ፤ “ዛሬ ሥልጣን ብንለቅ፤ እስከከ ዛሬ ድረስ ለፈጸምነዉ ወንጀል ሁሉ ጠጠያቂዮች ነን፡” በሚል ፍራቻ ብቻ ለሥልጣን ሳይሆን ከሕግ ለማምለጥ ሲሉ፤ እርሰዎን ወይም እንደአቶ ኃይለማርያም እንደእንዝርትና እንደ ዮዮ ለማሽከርከር ይሞክራሉ፤ ወይም በተቻላቸዉ መጠን በፍጥነት ከፖሊቲካው ጫዋታ ዉጪ በፍጥነት ለማሶጣት የተቻላቸዉ ከማድረግ እንደማይቆጠቡ እርሶዎም የሚዘነጉት አይመስለኝም።

ክቡር ዶክተር አብይ! ግን አይዞዎት፤ እግዚአብሔርና አንድ መቶ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ሕዝብ `ከጎነዎ ስለሆነ ከፊትዎ የቆመዉን ጎሊያድ እንዳይፈሩት።ከወያኔ መድፍና መትረየስ፤ የጦር አውሮጵላንና ሄሉኮፕተር፤ ታንክና የአጋዚ ጦር፤ የእግዚአብሔር ድጋፍና የኢትዮጵያ ሕዝብ የማያወላዉል ፍቅሩ ከኋላዎ ደጀን፤ ከፍተዎ ፊታውራሪ ሆኖ ይከተለዎታል። ይህ የዋሕና አማኝ ሕዝብ በርስዎ ላይ የጣለዉን ዕምነትና ፍቅር ብቻ አያጉድሉበት። ከርስዎ የሚጠብቀዉ ቆራጥኘትንና የማያወላዉ ጀግንነትን ነው። ባለመታደል ባለማወቅና በመንፈሰ ደካማነት ስድስት ዓመት ሙሉ፤ ወንበር ሲያሞቁና የወያኔ አፈቀላጤና ጉዳይ አስፈጻሚ አድርጎ እንደቀለደባቸዉ ሌላ አቶ ኃይለማርያም ይሆናሉ ብለን በጭራሽ አንገምትም። ያን የመሆንዝንባሌ ማሳየት የጀመሩ ዕለት በኢትዮጵያ ሕዝብና በርሰዎ መሃል ያለዉ ቃል ኪዳን ያን ዕለት ያቆማል። የኢትዮጵያን ሕዝብ ፍቅሩንና ወዳጅነቱን እንጂ ጸቡን አይመኙም። ይህ ቆራጥ ሕዝብ አንድ ጊዜ ፊቱን ካዞረበዎት መለስ ብሎ እንደማይመለከትዎት ይወቁ። ከጠላቱ ጎን ቆመዉ፤ለሚጠይቀዉ አንገብጋቢ ጥያቄዎቹ፤ በአፋጣኝ መልስ ከላገኘ ግን የተቀመጡበትን ዙፋን፤ የሾህ ወንበር ያደርገዋል።

ታላቅ ተስፋ የጣለብዎ፤ የሚወዱትና የሚወድዎ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከርሰዎ ባስቸኳይ እንዲፈጽሙለት የሚፍልጋቸዉን በቅደም ተከተል አሰፍራለሁ።ከገቡበትም፤የፖሊቲካ ማጥ ዉስጥ(Political quagmire)አውጥቶ፤ ከፊትዎ ሆኖ የተደነቀረዉን ጋሬጣም ፈጥኖ ያሶግድለዎታል ብዬ አምናለሁና በአንክሮ ይመልከቱት።

1ኛ/ የተረከቡትን የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣን ተጠቅመዉ የጊዜያዊ አዋጁን በፍጥነት እንዲያነሱለት፤

2ኛ/ በአገሪቷ ወሕኒ ቤቶች በዕስር ላይ የሚገኙ የፖሊቲካ እስረኞች ሁሉ፤አቶ አንዳርጋቸዉ ጽጌንም ጨምሮ በፍጥነት እንዲለቀቁልት፤

3ኛ/ የተዛባውና ያልተስተካከለዉ የኢትዮጵያ ሠራዊትና የደሕንነት አወቃቀር በፍጥነት፤ሁሉንም ብሔሮች ያካተተና የሚወክል ሆኖ እንደገና እንዲዋቀር ይጠይቃል፤

4ኛ/የሃገሪቷ ሕገ መንግሥት ፓርላማው መክሮበትና ዘክሮበት እንደገና ተስተካክሎ እንዲጻፍና አንቀጽ 39 ጨርሶ እንዲወጣ፤ ይጠይቃል፤

5ኛ/ በኢፊደሪ ፓርቲ ዉስጥ ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆኑ ሁሉ ነባር አባሎች የጡረታ መብታቸው ተከብሮ በፍጥነት ቦታዉን ለአዲሱ ትውልድ እንዲለቁ እንዲደረግም ያሳስባል፤

6ኛ/ በሰራዊቱ ዉስጥም የዕድሜ ገደብ ከ62 ዓመት እንዳይበልጥ በአዲሱ ሕገ መንግሥት ሕግ ሆኖ እንዲጸድቅ ያሳስባል፤

7ኛ/ ማንኛዉም የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን የኃላነት ሥራ ከመረከቡ በፊት፤ ያለዉን ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀስ የሃብቱ ዝርዝር፤ ከየት እንዴት እንዳፈራዉ ጭምር ዘርዝሮ እንዱያስረዳና እንድያስመዘግብ

8ኛ/ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ ከአማካሪዎቻቸዉ ጋራ መክረዉና ዘክረዉ፤ በፍጥነት የሽግግር መንግሥት እንዲቁቋምና ቀጥሎም የሕዝብ ምርጫ በቅርብ ጊዜ ዉስጥ እንዲያደርግና ለመጀመሪያ ጉዜ ያልተበረዘና ያልተከለሰ ምርጫ እንዲደረግና እስከዛሬ ድረስ “ምርጫ ቦርድ የሚባለዉ በወያኔ እጅ ተጠፍጥፎ የተሰራ በመሆኑ በፍጥነት ዲዞልቭ እንዲደረግ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይጠይቃል።

ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር! እነዚህ ከሕዝብ የቀረቡ ጥያቄዎች በፍጥነት መልስ እስከሚያገኙ ድረስ የሕዝቡ ትግል ይቀጥላል። ቄሮም ሆነ ፋኖ፤ በሰላምም ሆነ መሥሪያ አንስቶ በየዱር ገደሉ የተሰምራዉ አርበምኛ ፤ ጩኸቱን የቅጥላል ፤ ተቃዉሞዉን ያፋፍማል፤ ትግሉን በበለጠ አጠናክሮ ይፋፋማል። ጀግናዉም ሠይፉን ወደ አፎቱ አይመልስም የፈረሱም ኮርቻ አያራገፍምና በጥብቅ እንዲታሰብበት እጠይቃለሁ።

በመጨረሻም፤ ለአገራችንን ኢትዮጵያን፤ መሪያችንን እርሰዎንም፤ እኛንም ሕዝቦቿን፤ ሁሉን የሚችል አምላክ ይርዳን፤ ይባርከንም።

አሁንም ከፍ ባል አክብሮትና ትሕትና፤

ይፍሩ ኃይሉ
ኒው ሄቨን፤ ከነቲከት
ሰሜን አሜሪካ