ማንነትን መሰረት ያደረገ ህገ ወጥ ግድያና ሌሎች ሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች – የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ የቀደሙ ሪፓርቶች

 

በሶማሌ ክልላዊ መንግስት የሬርባሬና የዱቤ ጎሳዎች እራስን ባራስ የማስተዳደር ጥያቄ በመጠየቃቸው ምክንያት በሶማሌ ክልል ልዩ ሀይል ግድያና ማቁሰል ከመፈፀሙ በተጨማሪ 15 ሚ ብር የሚገመት እህል አውድመዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ በህግ ተመዝግቦ የሚንቀሳቀሰው የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ) በጥቅምት 23፤ 2007 አ.ም በ139ኛ እና በግነቦት 24፤ 2008 አ/ም 141ኛ ልዩ መግለጫው በሶማሌ ክልል እና ትግራይ ክልል ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት በዜጎች ላይ መፈጸሙን ይፋ አድርጎ ነበር፡፡

ሶማሌ ክልል

በሶማሌ ክልላዊ ብሄራዊ መንግስት በቀላፎና ሙስታሂል ወረዳዎች ታህሳስ 01 እና 02/2006 ብቻ 65 ሰዎች መገደላቸውን ሰመጉ 139ኛ ልዩ መግለጫው አሳውቋል፡፡ እንደሪፖርቱ መግለጫ ግድያውን የፈጸመው የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ነው፡፡ ግድያው ከ4 አመት ህጻን አንስቶ በሁሉም የእድሜ ክልል የሚገኙ ዜጎች ላይ ተፈጽሟል፡፡

በተጠቀሰው ቀናት ከግድያው ባሻገር በርካቶች በክልሉ ልዩ ኃይል በጥይትና በድብደባ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ልዩ መግለጫው 115 ሰዎች የተለያየ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው መዝግቧል፡፡

የክልሉ ልዩ ኃይል በተጠቀሱት ወረዳዎች የሬርባሬ ጎሳ አባላት ላይ ግድያና የአካል ጉዳት ከመፈጸሙም በላይ በሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረትም አውድሟል፡፡ ሰመጉ ልዩ መግለጫውን ለማዘጋጀት ተጎጂዎችን እና የተጎጂ ቤተሰቦችን ማነጋገሩን እና በቦታው ተገኝቶ ጉዳቱን መመልከቱንም አስፍሯል፡፡

ትግራይ ክልል

ሰመጉ ‹‹የማንነት ጥያቄ በሚያነሱ ዜጎች ላይ የሚፈፀም ግድያ፣ ህገ ወጥ እስር፣ አፍኖ መሰወር፣ ማፈናቀልና ንብረት መንጠቅ በአስቸኳይ ይቁም›› በሚል ግንቦት 24/2008 ባወጣው 141ኛው ልዩ መግለጫው፣ በትግራይ ክልል ወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ በማንሳታቸው 34 ሰዎች በአካባቢው የህወሓት አመራሮችና የክልሉ መንግስት የጸጥታ ሰዎች ግድያ እንደተፈጸመባቸው አስፍሯል፡፡ ከእነዚህ መካከል ዘጠኙ ከማንነት ጥያቄው ጋር በተያያዘ ለእስር ተዳርገው በእስር ቤት እያሉ ህይወታቸው ያለፈ ናቸው፡፡

ልዩ መግለጫው 47 ሰዎች ታፍነው ተወስደው የት እንደገቡ የማይታወቁ ስለመሆኑም በጥናት ማረጋገጡን ጠቅሷል፡፡ ሰመጉ በአማራ ማንነት ጥያቄ አቅራቢዎች ላይ ድብደባና ማሰቃየት፣ አስገድዶ መድፈር፣ እስራት፣ አድሎና አስተዳደራዊ በደል፣ የመሳሪያ ንጥቂያ፣ እዲሁም ከእርሻ መሬት ማፈናቀልና ቤት ንብረት ንጥቂያ እንደተፈጸመ በልዩ መግለጫው ገልጹዋል፡፡

አማራ ክልል፣

በተመሳሳይ በአማራ ክልል የቅማንት ማንነት ጥያቄ ባነሱ ሰዎች ላይም የመብት ጥሰት መፈጸሙን ሰመጉ በዚሁ በ141ኛው ልዩ መግለጫ ግልጹዋል፡፡ በዚህም በአማራ ክልል የጸጥታ ኃይሎችና ታጣቂዎች 22 ሰዎች ላይ ህገ ወጥ ግድያ ሲፈጸም በ10 ሰዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት መድረሱን መግለጫው አስፍሯል፡፡

ደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ክልል፣

ሰመጉ በዚሁ ልዩ መግለጫው ላይ በተመሳሳይ በደቡብ ክልል የቁጫ እና የኮንቶማ ማህበረሰቦች የማንነት ጥያቄ በማንሳታቸው የተለያየ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንደተፈጸመባቸው አብራርቷል፡፡

ሰመጉ ከማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ግጭቶችን ለመፍታት የኢፌዲሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 39 በሚደነግገው መሰረት ‹‹ራስን በራስ የማስተዳደር መብት›› መከበር እንደሚገባው አሳሰቧል፡፡ በዚህም የማንነት ጥያቄዎችን ተከትሎ የሚወሰደው የኃይል እርምጃ እና የሰብአዊ መብት ጥሰት በማናቸውም መልኩ ተቀባይነት እንደሌለው ሰመጉ ግለጹዋል፡፡ በመሆኑም መንግስት በህገ ወጥ ድርጊት ፈጻሚዎች ላይ አስፈላጊው የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ፣ ተጎጂዎችም ካሳ እንዲያገኙ፣ የተፈናቀሉ እንዲመለሱ እና ንብረት የተወሰደባቸው እንዲመለስላቸው አሳስቧል፡፡

ሙሉ ሪፖርቱን ከሰብአዊ መብቶች ጉባዬ ድረገፅ www.ehrco.org ላይ ወይም 139ኛውን ልዩ መግለጫ  እንዲሁም 141ኛውን ልዩ መግለጫ በመጫን ማውረድ ይችላሉ።