ወልቃይት በታሪክም በባህልምየአማራ አካል ነበረ (ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ)

“ወልቃይት በታሪክም በባህልምየአማራ አካል ነበረ” ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ (በምስረታ ላይ ያለው የአማራ ፓርቲ አደራጅ ኮሚቴ አባል)

ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ በ‹‹ተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር›› ትምህርት መስክ ሶስተኛ ዲግሪ (ፒ.ኤች.ዲ) ያላቸው ሲሆን በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ በረዳት ፕሮፌሰርነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡

ዕድሜያቸው ገና 40ዎቹን የጀመሩ ቢሆንም ከቀለምና ከታላላቆቻቸው ባገኟቸው የእውቀት መስኮቶች በመጠቀም ዘርፈ ብዙ ልምድ ያላቸው ምሁር ናቸው፡፡ እኒህ ምሁር በአሁኑ ወቅት በቅርቡ ይመሰረታል ተብሎ የሚጠበቀውን ‹‹የአማራ ህዝብ ፓርቲ›› የመስራች ኮሚቴ አባል ሆነው እየሰሩ ሲሆን በቅርቡም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጥሳችሁ ተሰብስባችኋል ተብለው ከ18 ጓደኞቻቸው ጋር ለ15 ቀናት በባህርዳር ከተማ እስር ላይ ቆይተዋል፡፡

የአካባቢው ኮማንድ ፖስት በቁጥጥር ስር ባዋላቸው ወቅት በደህንነት ሃይሎች ድብደባ እንደተፈጸመባቸው እና ወደክልሉ የክልሉ ጸጥታ ሀይሎች ከተዘዋወሩ በኋላ ግን ተገቢው እንክብካቤ እንደተደረገላቸው የሚናገሩት ወጣቱ ምሁር እና ፖለቲከኛ ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ በወቅታዊ ጉዳዮች እንዲሁም ስለሚመሰርቱት የአማራ ፓርቲ እና ስለ ወልቃይት ጉዳይ ከሸገር ታይምስ ጋር ያደረጉትን ቆይታ ከዚህ በታች አቅርበነዋል፡፡

(👉 ይህ ቃለ ምልልስ በሸገር ታይምስ ቅፅ 02 ቁጥር 31 የታተመ ነው።)

ሸገር ታይምስ፡- በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ እንዴት ያዩታል?

ዶክተር ደሳለኝ፡- አሁን አገራችን ያለችበት ሁኔታ ሁላችንም እንደምናውቀው በጣም አስቸጋሪ የፖለቲካ ፈተና እና የፖለቲካ አቋራጭ መንገድ ላይ ነች፡፡ በአጠቃላይ በጣም አሳሳቢ ወቅት እንዳለች ነው የሚሰማኝ፡፡

ሸገር ታይምስ፡- የአማራ ፓርቲ ለቋቋም ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፈቃድ አግኝታችሁ ፓርቲ ለማደራጀት እየተንቀሳቀሳችሁ መሆኑ ቀደም ሲል ተዘግቦ ነበር፡፡ አሁን እንቅስቃሴያችሁ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
ዶክተር ደሳለኝ፡- አሁን በምንፈልገው መስፈርት መሰረት የመስራች አባላትን ፊርማ እያሰባሰብን እና አባላትን ምልመላ ላይ ነው የምንገኘው፡፡ ይህንን እንደጨረስን ደግሞ የመስራች ጉባዔውን እናካሂዳለን፡፡ አሁን እየሰራን ያለነው በምስረታውና ቅድመ ምስረታው ላይ ትኩረት አድርገን ነው፡፡

ሸገር ታይምስ፡- በዚህ መሃል ግን ለ15 ቀናት አካባቢ ለሚሆን ጊዜ እርስዎን ጨምሮ 18 የቡድናችሁ አባላት ለእስር ተዳርጋችሁ ነበር፡፡ ለእስር የዳረጋችሁ ክስ ምንድነው የእስር ቤት ቆይታችሁስ ምን ይመስላል?

ዶክተር ደሳለኝ፡- ያኔ ተላልፋችሁታል የተባልነው ጥፋት ተብሎ የተነገረን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመተላለፍ ህዝባዊ ስብሰባ ማድረግ እና ከሶስት በላይ ሆኖ ተሰብስቦ መገኘት እንዲሁም ያተፈቀደ ስብሰባ ማድረግ የሚል ነው፡፡ እኛ ያልነው በጊዜው ያደረግነው መሰባሰብ መደበኛ ያልሆነ መገናኘት እንጂ መደበኛ ስብሰባ ወይም የአደባባይ ሰልፍ እና ስብሰባ አላካሄድንም የሚል ነበር፡፡ መጀመሪያ ከብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት ነን ብለው የያዙን ሰዎች በብዙዎቻችን ላይ ድብደባ ፈጽመውብን ነበር፡፡ ከእነሱ ወደ ክልሉ ጸጥታ ሀይሎች ከተሸጋገርን በኋላ ግን ጥሩ የሚባል አያያዝ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ክብራችንን ጠብቀው የምንፈልገውን አድርገውልናል፡፡

ሸገር ታይምስ፡- በኢትዮጵያ ህገ መንግስት አንቀጽ 30 ላይ ‹‹ማኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሳሪያ ሳይዝ በሰላም የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት አለው፡፡ ከቤት ውጭ የሚደረጉ ስብሰባዎችና ሰላዊ ሰልፎች በሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎች በህዝብ እንቅስቃሴ ላይ ችግር እንዳይፈጥሩ ለማድረግ ወይም በመካሄድ ላይ ያለ ስብሰባ ወይም ሰላማዊ ሰልፍ ሰላምን፣ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን እና የህዝብን የሞራል ሁኔታ እንዳይጥሱ ለመጠበቅ አግባብ ያላቸው ስርዓቶች ሊደነገጉ ይችላሉ›› ሲል ያስቀምጣል፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከዚህ ህግ ጋር ይጣረሳል የሚሉ ፖለቲከኞች አሉ፡፡ በእናንተ እይታስ እንዴት ትመለከቱታላችሁ?

ዶክተር ደሳለኝ፡- አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በህገ መንግስቱ ለዜጎች የተሰጡና የተደነገጉ በርካታ መብቶችን የሚከለክል እና የክልከላው ስፋቱ እና ወሰኑ በራሱ የት ድረስ እንደሆነ በግልጽ የማያሳይ እንዲሁ በድፍኑ ምንም ነገር አታድርጉ የሚል አዋጅ መሆኑ በጣም አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ አገራችን አሁን ለገባችበት የፖለቲካ ቀውስም መፍትሔ ለማበጀት እኛን ጨምሮ ጥረት ለሚያደርጉ አካላት መፈናፈኛ እና መንቀሳቀሻ የሚያሳጣ በጣም አስቸጋሪ ሆኖ ነው ያገኘነው፡፡ በአጠቃላይ ለእኛ በጣም ከባድ ነው፡፡

ሸገር ታይምስ፡- እናንተ የተያዛችሁት የት እና ምን እያደረጋችሁ ነው?
ዶክተር ደሳለኝ፡- ውይይታችን ሰው እንዳይረብሽ እና ስብሰባ ተደረገ ተብሎ ትኩረት እንዳንስብ ጣና ሀይቅ ላይ በጀልባ ሆነን ስንወያይ ውለን ውይይታችንን ጨርሰን ለእራት ከጀልባ እየወረድን ባለንበት ሰዓት ነው የተያዝነው፡፡

ሸገር ታይምስ፡- ፓርቲ ለማቋቋም ከምርጫ ቦርድ ፈቃ የተሰጣችሁና እየተንቀሳቀሳችሁ ያላችሁት ብሔር ላይ መሰረት ያደረገ ፓርቲ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ዘውግን መሰረት ያደረገ ፓርቲ ማቋቋም ለምን አስፈለገ?

ዶክተር ደሳለኝ፡- የኢትዮጵያ ሁኔታ ከ1983 ዓ.ም ወይም ከሽግግሩ ወቅት ጀምሮ አደረጃጀቱ ብሔርን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ክልሎች አደረጃጀታቸውም ሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ አብዛኞቹ ፓርቲዎች አደረጃጀታቸው ብሔርን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው የአማራው ብሔር ለረጅም ጊዜ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነትን የሚያምን እና በኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ውስጥ ታግዬ መብቶቼና ጥቅሞቼ ይከበሩልኛል ብሎ የሚያስብ ህዝብ ነው፡፡ በብዙ የአንድነት ሀይሎች ውስጥም በንቃት ይሳተፍ የነበረው አማራው ነው፡፡ ያ ሁኔታ ግን አሁን ባለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አማራ ብቻውን ለህብረ ብሔራዊ አንድነት እና በአንድነት የፖለቲካ አሰላለፍ ውስጥ ተሳትፎ ጥቅሞቹን ማስከበር እንደማይችል እንዲሁም የሚጮህለት ፓርቲ እንደጠፋ ታይቷል፡፡ በዚህ የተነሳም የአገሪቱ ህግ በሚፈቅደው መሰረት የአማራን ህዝብ ጥቅሞች፣ ፍላጎቶች እና ጥያቄዎች የሚያንጸባርቅ ፓርቲ አስፈላጊም ነው ተገቢም ነው፡፡ ሌላው በብሔሩ ተደራጅቶ አማራ በብሔርህ አትደራጅ የሚል ብዙ ሙግት እንሰማለን፡፡ በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ የታገለለት አካል ግን አልነበረም፡፡ ይህን ሙግት የሚያቀርቡትም የአገሪቱን ተጨባጭ የፖለቲካ ሁኔታ ያልተገነዘቡ ናቸው እንጂ አማራ እስካሁን በዚህ ስርዓት ይሄን ያህል ግፍና መከራ የደረሰበት በብሔሩ እና በማንነቱ ስላልተደራጀ ነው፡፡

ሸገር ታይምስ፡- የእናንተ ፓርቲ ለመመስረት እንቅስቃሴ ላይ መሆኑን ተከትሎ አስተያየታቸውን የሚሰጡ ምሁራን ‹‹በዚህ ዘመን ዘውግ ላይ ትኩረት ያደረግ ፓርቲ በአማራ ክልል መቋቋሙ በኦሮሚያ እና በትግራ ክልል እንዳሉት ነጻ አውጭ ድርጅቶች ሌላ ጽንፍ ይዞ ይመጣል፡፡ ከዚህ ይልቅ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ተቀላቅለው ጥንካሬ ቢፈጥሩ ይሻላል ሲሉ ይናገራሉ፡፡ በዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድን ነው?

ዶክተር ደሳለኝ፡- አንደኛ የአማራ ብሔር እንቅስቃሴ እና የአማራ የፖለቲካል ጥያቄ ይዘን የአማራን ህዝብ ይዘን እናታግላለን ስንል የመገንጠል ጥያቄ ዓላማችን አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ የተፈጠረችው በአባቶቻችን ደም፣ አጥንትና የህይወት መስዋዕትነት ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ልንገነጠል አንችልም አንፈልግምም፡፡
ይህ ማለት ግን አማራ ብብሔሩ ተደራጅቶ እንደ አማራ እየተጎዳ እና እየተጠቃ ያለበትን የፖለቲካ ሁኔታ ተቀብሎ ዝም ብሎ ህብረብሔራዊ ድርጅቶች ውስጥ ሊቀጥል ይችላል ማለት አይደለም፡፡ በግልጽ መናገር የምፈልገው ህብረ ብሔራዊ ፓርቲዎች ቢጠነክሩ እኛ ተቃውሞ የለንም፡፡ በሚያሰራን በአማራ ህዝብ ጥቅም፣ ደህንነትና መብት ዙሪያ እና በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ማበብ ዙሪያ ተባብረን እንሰራለን፡፡ ግን ደግሞ መረሳት የሌለበት ነገር አማራ ባለፉት የዚህ ስርዓት የአገዛዝ ዓመታት ሲታሰር፣ ሲገደል፣ ለዘመናት ከኖረበት የአገሩ ክፍል ሲፈናቀል እና ሲዋረድ የጮኸለት የፖለቲካ ፓርቲ አልነበረም፤ ህብረ ብሔራዊ ፓርቲዎች ውስጥ ይሳተፉ የነበሩ አማሮችን ሌሎች ብሔሮችን ላለማስቀየም በሚል ሰበብ በደምሳሳው ዝም ብለው አንገታቸውን ደፍተው የሚያልፉበት የፖለቲካ ተሞክሮ አማራን ተጎጂ ያደረገ ስለሆነ ይህ ለአማራ አዋጭ አይደለም፡፡ ስለዚህ አማራ በብሔሩ ተደራጅቶ እንደ አማራ እየተጠቃ ያለበትን ሁኔታ መመከት፣ መቋቋም እና ለመብቱ መታገል ተገቢም አስፈላጊም ነው ብለን እናምናለን፡፡

ሸገር ታይምስ፡- አማራ ከሚጠይቃቸው ጥያቄዎችና ጥቅሞች መካከል የግዛትና የማንነት ጥያቄዎች ይገኙበታል፡፡ በተለይ የወልቃይት ጉዳይ ትልቁ ትኩረት የተሰጠው እንደሆነ የአማራ አክቲቪስቶች ደጋግመው ይገልጹታል፡፡ በእናንተ ፕሮግራም ላይ የወልቃይት ጉዳይ እንዴት ነው የሚስተናገደው?

ዶክተር ደሳለኝ፡- ፕሮግራማችን ገና አልጸደቀም፤ በግሌ የእኔ እምነት ግን የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ ህጋዊና ህገ መንግስታዊ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ህገ መንግስት በተደነገገው የማንነት ጥያቄ መሰረት የቀረበ ጥያቄ ነው፡፡ ወልቃይት በታሪክም በባህልም በብዙ አስተዳደራዊ ሂደቶችም ውስጥ የአማራ አካል የነበረ ከጎንደር አማራ ጋር ትልቅ መተሳሰር ያለው እና ራሳቸውንም አማራ ነን ብለው የሚገልጹ ስለሆነ ህጋዊ ጥያቄ ነው፡፡ ያ ህጋዊ ጥያቄ ደግሞ ህጋዊ መልስ ሊሰጠው ይገባል፡፡
ስለዚህ የወልቃይት ህዝብ በተለይ ከ1983 ዓ.ም በፊት ህወሓት አካባቢውን በሀይል ተቆጣጥሮ ማንነታቸው ላይ ጫና እስከሚያደርስባቸው ድረስ ማንነታቸውን የሚገልጹት እንደ ጎንደር አማራ ነበር፡፡

ሸገር ታይምስ፡- ኢትዮጵያ በብዙ ችግሮች ውስጥ መሆኗን ቀደም ብለው ነግረውናል፡፡ ለዚህች አገር ሰፊ ችግር ዘላቂ መፍትሔ ይሆናል ብላችሁ በፕሮግራም ደረጃ የያዛችሁት ሀሳብ ምንድን ነው?

ዶክተር ደሳለኝ፡- አሁን ባለው ሁኔታ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር ምንጩ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በተለይም የኢህአዴግ ዋና አንቀሳቃሽ ህወሓት ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የኢትዮጵያ ህዝብ የዴሞክራሲ፣ የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የመልካም አስተዳደር እና የልማት ጥያቄ አለው፡፡ ወደ አማራ ስትመጣ ደግሞ የህልውና እና የማንነት ጥያቄዎች አሉት፡፡ አማራ በመሆኑ ብቻ አደጋ ገጥሞኛል ብሎ ስለሚያስብ የህልውና ጥያቄ ያነሳል፡፡ ለእነዚህ ጥያቄዎች ደግሞ ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈልጋሉ፡፡ ስለዚህ ገዥው ፓርቲ ከሁሉም የኢትዮጵያ ጉዳይ ያሳስበናል እና በአገሬ ድርሻ አለኝ ብለው ከሚያስቡ የፖለቲካ ሀይሎች ጋር ድርድር ማድረግ ያስፈልገዋል፤ በሰላማዊ መንገድ ውይይት መክፈት እና ሰላማዊ ወደሆነ ሽግግር መሄድ ኢትዮጵያን ለማዳን የገዥው ፓርቲ ግዴታ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ሌሎች የፖለቲካ ሀይሎችም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በመታገል ገዥውን ፓርቲ ማስገደድ እና ሰላማዊ ወደሆነ የፖለቲካ መፍትሔ መሄድ አስፈላጊ ነው፡፡

ሸገር ታይምስ፡- የአማራ ክልል ገዥ ፓርቲ ብአዴን መሆኑ ይታወቃል፡፡ እናንተም በብሔሩ ህዝብ ስም ተደራጅታችሁ ስትመጡ ብአዴንን ለመገዳደር መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ብአዴን ለብሔሩ ተወላጆች ዴሞክራሲያዊና የልማት መብቶች መከበር ላይ ያያችሁበት ድክመት ምንድን ነው?

ዶክተር ደሳለኝ፡- ብአዴን እስካን በነበረው ሁኔታ ከአመሰራረቱም ጀምሮ በመስራች አባላቱም ከአማራ ህዝብ ጋር ያለው ትስስርም መሰረት አድርጎ የሰራቸው በጎ ነገሮች አሉ፡፡ ነገር ግን እንደእኔ እይታ ሊቀርፋቸው የሚገባ ብዙ ድክመቶች አሉበት፡፡ ለምሳሌ ከክልሉ ውጭ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አማሮች በሚኖሩባቸው ክልሎች ምንም አይነት የፖለቲካ ውክልና የላቸውም፤ ለመብታቸው የሚከበርላቸውና መብታቸውን የሚጠይቅላቸው አካል የለም፡፡

ብአዴን እነዚህን ጥያቄዎች አማራ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ሌሎች ብሔሮች ራስን በራስ የማስተዳደር፤ በክልሉ ፓርላማ ውስጥ ውክልና የማግኘት፣ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጥያቄዎቻቸው እንዲመለሱ በተደረገበት ሁኔታ በሌሎች ክልሎችም የሚኖሩ አማሮች እነዚህ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው መታገል አለበት፡፡

የልማት ተጠቃሚነቱን ስናየውም በዓለም ላይ በጣም ድሃ የሚባል ህዝብ ያለበት፣ የመሰረተ ልማት ተጠቃሚነትም ከሌሎች ክልሎች ጋር ስናየው በጣም ወደኋላ የቀረበት፣ ትምህርት ቤቶቻችንም መቀመጫ የሌላቸውና በዳስ ውስጥ ተማሪዎችን የሚስተምሩ እንዲሁም በሌሎች መስኮችም ወደኋላ የቀረ ክልል ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህን ነገሮች በአግባቡ ለይቶ መፍትሔ የመፈለግና ለዚህ ደግሞ የአገሪቱ ገዥ ፓርቲ በሆነው ኢህአዴግ ውስጥ ያለውን ድርሻ ተጠቅሞ የመታገል እና ጥያቄዎቹን የማራመድ ግዴታ አለበት፡፡

ሸገር ታይምስ፡- ስለዚህ በእናንተ እይታ ብአዴን በድክመት የተሞላ ፓርቲ ነው ብላችሁ ታምናላችሁ?

ዶክተር ደሳለኝ፡- እስካሁን ያሉት በድክመት የሚነሱ ናቸው፡፡ አሁን ግን በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታዩ ያሉ ብአዴን ውስጥ ለህዝባቸው የሚቆረቆሩ ተስፋ ሊጣልባቸው የሚችሉ እንቅስቃሴዎችና ግለሰቦች እየመጡ ነው፡፡ እነዚህን ግለሰቦች ባሉበት ሆነው የአማራን ህዝብ ጥቅምና መብት እንዲያስከብሩ ማበረታታት ያስፈልጋል፡፡ ግን ደግሞ በሚገባው ደረጃ እነ ህወሓት እና ኦህዴድ አሁን ባሉበት ደረጃ ጠንክሮ ሰፊውን የአማራ ህዝብ ፍላጎት ይዞ መቅረብ እና መታገል አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡

ሸገር ታይምስ፡- ለምትመሰርቱት ፓርቲ የተሰጠው ስያሜ ማን ይባላል? በመጨረሻም መናገር የሚፈልጉት ነገር ካለ እድሉን እንስጥዎ

ዶክተር ደሳለኝ፡- የእኛ እንቅስቃሴ ከታወቀ በኋላ ብዙ ሰዎች አማራ በብሔሩ ልደራጅ ማለት ኢትዮጵያን እንደሚያፈርስ፣ እንደሌሎች አፍራሽ ብሔርተኞች የአማራ ህዝብ ሊገነጠል ነው፣ እንዲሁም የአማራ ህዝብ ጥያቄም ሆነ ልናቋቁም ያሰብነው ፓርቲ ለኢትዮጵያ አደጋ አለው ብለው በስህተት የተረዱን እንዳሉ ትንሽም ቢሆን እንሰማለን፡፡ ይሄ ስህተት እና መታረም ያለበት ነገር ነው ፡፡ አማራ አባቶቹ በሰሩለት አገር ማንነቱ እና ታሪኩ ተጠብቆና ተከብሮለት ከሌሎች ብሔሮች ወንድም እህቶቻችን ጋር በእኩልነት ላይ ተመስርቶ እንዲኖር እንፈልጋለን፡፡

ለዚህ ደግሞ አሁን ያለው ሁኔታ ያን ስለፈቀደለት ብቻ ህልውናችንን ለማስከበር ተገደን የገባንበት መሆኑን የአማራ ህዝብም ሆነ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያውቀው እንፈልጋለን፡፡ ብዙ የአማራ ምሁራንና የተለያየ የህብረተሰብ ክፍሎችም ከጎናችን ተሰልፈው ለህዝባችን ህልውና በጋራ መፍትሔ ለማበጀት ተገቢው ወቅት ነው ብለን እናስባለን፡፡ ይህ በደንብ እንዲታወቅልን እንፈልጋለን፡፡ ስለ ስያሜው ለተነሳው ጥያቄ ስያሜያችን እስካሁን ይህ ነው ተብሎ አልጸደቀለትም፡፡ ብዙ ስያሜዎች ስለቀረቡ አንዱን መምረጥ የሚቻለው በምስረታ ጉባዔው ላይ ይሆናል፡፡