የሙሴ + አሮንና ኦር = ድል (ዳንኤል ክብረት)

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙ የመሪና የተባባሪ ድርሻን ከሚገልጡ ታሪኮች አንዱ የሙሴና፣ የአሮንና የሖር ታሪክ ነው(ዘጸ. 17÷8-16)፡፡

አማሌቃውያን ከእስራኤል ጋር ሲዋጉ ኢያሱ ጎልማሶቹን ይዞ ከአማሌቃውያን ጋር ይዋጋ ነበር፡፡ ሙሴ ደግሞ ወደ ኮረብታው ወጣ፡፡ ሙዜ እጁን ባነሣ ጊዜ እስራኤል ድል ያደርጋሉ፡፡ ሙሴ ደክሞት እጁን ባወረደ ጊዜ ደግሞ አማሌቅ ድል ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ሙሴ ቀኑን ሙሉ ዋለ፡፡ በመጨረሻ ግን የሙሴ እጆች ከበዱ(ደከሙ)፡፡ ይህን የተመለከቱት አሮንና ሖር ለሙሴ የድንጋይ ወንበር አዘጋጁለት፤ ሙሴም እዚያ ድንጋይ ላይ ተቀምጦ እጁን ዘረጋ፡፡ ድሉም ለእስራኤል ሆነ፡፡ ነገር ግን አሁንም ሙሴ እጆቹ እየደከሙ መጡ፡፡ አሮንና ሖርም በግራና በቀኝ ሆነው የሙሴን እጆች ከፍ አድርገው ደገፏቸው፡፡ ያን ጊዜ ሙሴ እጆቹን አነሣ፡፡ እስራኤልም አማሌቅን ፈጽመው ድል አደረጉ፡፡

አንድ መሪ ውጤታማ የሚሆው ብቻውን አይደለም፡፡ እንኳንና በሰዎች የተመረጠ መሪ እግዚአብሔር የመረጠው ሙሴ እንኳን ብቻውን ውጤታማ መሆን አልቻለም፡፡ መሪ ምን ጠቢብ፣ ጎበዝ፣ ውጤታማ፣ ተወዳጅና ዐቅም ያለው ቢሆንም እንኳን እንደ ሙሴ እጆች መዛሉ አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህም እንደ አሮንና እንደ ሖር መንገዱን አይቶ የሚደግፈው ይፈልጋል፡፡ መልካም መሪ ውሳኔዎቹ፣ የለውጥ ሐሳቦቹ፣ ዕቅዶቹና ቃል ኪዳኖቹ ተግባራዊ እንዲሆኑ የሚያበረቱት አሮንና ሖር ይፈልጋል፡፡ አሮንና ሖር ለሙሴ የተሰጠው አልተሰጣቸውም፡፡ ነገር ግን ሙሴን ደግፈው የሚፈልጉትን ውጤት አመጡ፡፡ ሁሉም ሰው መሪ ባይሆንም
የመልካም መሪን ሐሳብ፣ ዕቅድ፣ ራእይና ውሳኔ በመደገፍ ግን ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡

ሁሉም ሰው ደራሲ ባይሆንም የደራሲውን እጆች መደገፍ ግን ይችላል፡፤ ሁሉም ሰው ተመራማሪ ባይሆንም የተመራማሪውን እጆች ግን መደገፍ ይችላል፡፡ ሁሉም ሰው የበጎ አድራጎት ማኅበር መመሥረት ባይችልም የበጎ አድራጎት ማኅበራቱን እጆች መደገፍ ግን ይገባል፡፡ ሁሉም ሰው የፖለቲካ ፓርቲ መመሥረት አይገባውም፡፡ የፓርቲዎቹን እጆች መደገፍ ግን ይቻላል፡፡ ሁሉም ሰው ሐሳብ ላያመነጭ ይችላል፡፡ የሐሳብ አመንጭዎችን እጆች ግን መደገፍ ይገባል፡፡ ሁሉም ሰው ታጋይ ላይሆን ይችላል፤ የታጋዮችን እጆች መደገፍ ግን ይገባል፡፡

ሙሴ አንድ ደጋፊዎቹ ግን ሁለት ነበሩ፡፡ ምንጊዜም ከደጋፊዎች ተደጋፊዎች ያንሳሉ፡፡ ታሪክ እንደሚያስተምረን ዓለምን የለወጧት ጥቂት ባለ ተሰጥዖዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን ሐሳባቸውን፣ መንገዳቸውን፣ ድርሰታቸውን፣ ምርምራቸውን፣ ሙከራቸውን፣ አመራራቸውን፣ ትምህርታቸውን፣ ጥረታቸውን የሚደግፉ ተቋማት፣ ግለሰቦች፣ ሚዲያዎች፣ መንግሥታትና ማኅበረሰቦች በማግኘታቸው ውጤታማዎች ሆኑ፡፡

ብዙ ሙሴዎች አሮንና ሖርን አጥተው እጃቸው ዝሎ ድል ሆነዋል፡፡ መንገዱ፣ ሐሳቡ፣ ውጣ ውረዱ፣ ሙግቱ፣ ጭቅጭቁ፣ የሰው ትችትና ወቀሳ፣ ስድብና ዕንቅፋትነት አዝሏቸው ድል ከማድረግ ድል ወደመሆን ወርደዋል፡፡ ክብሪቱን የሚያግዙት እንጨቶች ጠፍተው ቦግ ብሎ ጠፍቷል፡፡ በታሪካችን ብዙ ሙሴዎች መጥተው ነበር፡፡ ነገር ግን የሚያግዛቸውና ክንዶቻቸውን የሚደግፍ፤ ቢያንስ የድንጋይ መቀመጫ እንኳ የሚሰጥ አጥተው በሞትና በሽፈት ድል እየሆኑ ተገቢውን ለውጥ ሳያመጡ ቀርተዋል፡፡

ድል የማድረጊያ አንዱ መንገድ ብርቱዎቹን መደገፍ ነው፤ ክንዳቸው፣ ድምጻቸው፣ ሥራቸው፣ ጥረታቸው፣ ሐሳባቸው፣ ትግላቸው፣ ከፍ ሲል ድል የሚያደርጉትን መደገፍ ነው፡፡ መጥፎ ሠሪዎችን ከምንቃወመው በላይ መልካም ሠሪዎችን የማንደግፍ ከሆነ ውጤት አናመጣም፡፡

የሙሴም ታላቅነት ምን መሪ፣ እጆቹ ታላቅ ሥራ የሚሠሩና ድል አድራጊ ቢሆንም ሊደክም፣ ሊሸነፍ፣ ሊያቅተውና ሊዝል እንደሚችል አመነ፡፡ ያለ ሌሎች ድግፋ ብቻውን ለውጥ እንደማያመጣ ተቀበለ፡፡ ታላቅነት ማለት የታናናሾችን አስተዋጽዖ መናቅ አይደለም፡፡ ሁሉን ብቻዬን አደርገዋለሁ አላለም፡፡ አሮንና ሖር እንደሚያስፈልጉት ተቀበለ፡፡ ጎበዝ ሰው እንዲህ ነው፡፡ ሁሉንም ለብቻዬ እችለዋለሁ አይልም፡፡ የአንድ ሰው ውጤታማነት የብዙ ሰዎች አስተዋጽዖ ውጤት ነውና፡፡ ድል የሙሴም፣ የአሮንና የሖርም የየብቻ ውጤት አይደለም፡፡ ድል የሙሴ፣ የአሮንና የሖር የኅብረት ውጤት ነው፡፡