መጪው ምርጫ፤ የተበላ ዕቁብ? (ሳምሶን ኀይሌ)

ከሳምሶን ኀይሌ

ዶ/ር ዐቢይን ሊቀመንበር አድርጎ በመምረጡ ኢሕአዴግ ድኗል፤ መጪውን ምርጫም በሰፋ የድምጽ ልዩነት ያሸንፋል፡፡ የክርክሬ ፍሬ ነገር ይኽ ነው፡፡

በኢሕአዴግ ውስጥ በተደረገው የሥልጣን ሽግሽግ እና ለውጡ በኅብረተሰቡ ዘንድ ባስገኘው ከፍ ያለ የተስፋ ስሜት ምክንያት ገዥው ግንባር መጪውን ብሔራዊ ምርጫ በሰፋ የድምጽ ልዩነት ሊያሸነፍ እንደሚችል የተወሰኑ ነጥቦችን እንደ አብነት በማንሳት ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡ ጽሑፉ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ እያዘጋጀሁት ካለሁት ሰፋ ያለ ሐተታ ተቀንጭቦ የቀረበ ነው፡፡

ዕድለኛው ጠቅላይ ሚኒስትር እና የኢሕአዴግ ማገገም
***

ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ዕድለኛ ግለሰብ ናቸው፡፡ በኦሕዴድ ሊቀመንበርነታቸው፣ በኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድርነታቸው እና ስለ ኢትዮጵያዊነት ባላቸው “አቋም” ከፍ ያለ ተቀባይነት ያገኙት አቶ ለማ መገርሳ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አለመሆናቸው ለዶ/ር አብይ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን አስተዋጽዖው የጎላ ነው፡፡ ይኼ ትልቅ ዕድል ነው፡፡ ዶ/ር አብይ የኦሕዴድ ሊቀመንበር ሆነው ከተመረጡ በኋላ ደግሞ አብዛኛው ዜጋ ከሌሎች የግንባሩ ሊቀመንበሮች በተለየ መልኩ እሳቸው መመረጥ እንዳለባቸው ሲቀሰቅስና ፍላጎቱን (ምኞቱን) ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ ይህም ትልቅ ዕድል ነው፡፡ የኢሕአዴግ ሊቀመንበርና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በሆኑበት ወቅት የታየው የሕዝብ የደስታና የተስፋ ስሜት ከፍተኛ ነበር፤ አሁንም ያ የተስፋ ስሜት በሕዝቡ ውስጥ ይታያል፡፡ በሕዝብ ሳይመረጡ ይህን ያህል ድጋፍና ቅቡልነት (legitimacy) ማግኘት ትልቅ መታደል ነው፤ ዕድለኛነት፡፡

በቀሩት ኹለት ዓመት የማይሞሉ ጊዜያት የተበታተነው የተቃውሞ ጎራ ተሰባስቦ፣ ቢሮ ከፍቶ፣ ሕዝብ አደራጅቶና ፕሮግራሙን አስረድቶ፣ ምርጫ ቦርድ በገለልተኛነት ስለሚዋቀርበትና የምርጫ ሕጉ ስለሚሻሻልበት ሁኔታ ተደራድሮ ኢሕአዴግን ከሥልጣን ሊያወርድ የሚችለበት ዕድል በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ስለሆነም ኢሕአዴግ ከአራቱ ክልሎች ቢያንስ በሦስቱ አብላጫ ድምጽ ያገኛል፡፡ አራቱን ታዳጊ ክልሎችና ሐረሪን የሚመሩትን የግንባሩን አጋር ድርጅቶች የሚቀናቀን ተቃዋሚ ድርጅትም የለም፡፡ ምርጫው በኢሕአዴግ አሸናፊነት ይጠናቀቃል፡፡ እንዴት?

ኦሮሚያ ክልል፤
***

ዶ/ር ዐቢይ የአሮሚያ ክልል ወጣቶች ያነሱትን አመጽ ተከትሎ ኦሕዴድ የአመራር ለውጥ ሲያደርግ ወደ ፊት ከመጡት ባለሥልጣናት አንዱ ናቸው፡፡ የሕዝብ ተቃውሞ ውጤት ናቸው ማለት ነው፡፡ ስለሆነም የኦሕዴድ አባላትን ጨምሮ በርካታ ቁጥር ያለው ኦሮሞ ይደግፋቸዋል፡፡ በኦሮሞ ሰፊ ሕዝብም ሆነ በሕሩያኑ (elite) አካባቢ ሊኖር የሚችለው አስተያየት ዶ/ር ዐቢይ ሥልጣናቸውን በሚገባ (በነጻነት) የሚጠቀሙበት ሁኔታ ይመቻች የሚል ነው፡፡ ስለዚህ ኦሮሚያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱት ብሔራዊም ሆኑ ኅበረ-ብሔራዊ ድርጅቶች ያን ያህል ኦሕዴድን የሚያሸንፍ ድምጽ ሊያገኙ አይችሉም፡፡ እነ ዶ/ር መረራና አቶ በቀለ ገርባ (ኦፌኮ) ሲያቀርቡት የነበረው ጥያቄ የኦሕዴድ ጥያቄ ሆኗል፤ ኦሕዴድ የኦፌኮንም የኦነግንም አጀንዳ ተረክቧል ወይም ነጥቋቸዋል፡፡ ጥያቄውን መረከብ ብቻ ሳይሆን የመፍትሔ ምንጭም እየሆነ ነው፡፡ ስለሆነም የኦሮሞ ሕዝብ ከአቶ ለማ መገርሳ አቶ በቀለ ገርባን ወይም ከዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር መረራ ጉዲናን የሚመርጥበት ዕድል አለ ማለት ያስቸግራል፡፡ ስለሆነም ኦሕዴድ/ኢሕአዴግ ኦሮሚያ ላይ ያሸንፋል፡፡

ትግራይ ክልል፤
***
በየሕወሓት መሪዎች በኩል ከዚህ በኋላ ነገሮች እንዳለፉት 27 ዓመታት በሕወሓት ዛቢያ ዙሪያ እንደማይሽከረከሩና ሐቁን መጋፈጥ እንዳለባቸው ሳይወዱ በግዳቸው መቀበል እንዳለባቸው ብቻ ሳይሆን የዶ/ር ዐቢይ (ኦሕዴድ) ወደ ሥልጣን መምጣት መዳኛቸው እንደሆነም ግንዛቤ ተወስዷል፡፡ ሕወሓት ኢሕአዴግ ለረዥም ዓመታት በሥልጣን ላይ እንዲቆይ ካስፈለገ በግንባሩ አባል ድርጅቶች መካከል ያለው ግንኙነት በሂደት እየተስተካከለ (አባል ድርጅቶች ተመጣጣኝ አቅምና ተሰሚነት) መሄድ እንደሚገባው ተቀብሏል፡፡ በፌደራል ደረጃ ይኽን ነባራዊ ዕውነታ የተረዳው ሕወሓት የህልውናው መሠረት በሆነው ሕዝብና ክልል የልማት ተጠቃሚነት ላይ ሰፊ ሥራ ለመሥራት ትግራይ ላይ ከፍተኛ ትኩረት አድርጓል፡፡ ድርጅቱ ከዚህ በኋላ በሚሠራቸው ሥራዎች ብቻ ሳይሆን ከዚህ በፊት በሠራቸውና ከሕዝቡ ጋር ባለው ልዩ ታሪካዊ ቁርኝት ምክንያት ትግራይ ውስጥ ከፍ ያለ ተቀባይነት እንዳለው ግልጽ ነው፡፡

ስለሆነም ትግራይ ውስጥ በመጪው ምርጫ ከሕወሓት ጋር ተወዳድሮ ሊያሸንፍ የሚችል የፖለቲካ ድርጅት የለም፡፡ በክልሉ የሚንቀሳቀሰው አረናም አሁን ባለው ድርጅታዊ ቁመና ሕወሓትን ሊገዳደር የሚችል ድርጅት አይደለም፡፡ በዚህ ምክንያት ትግራይ ክልል ውስጥ እንደተለመደው ሕወሓት/ኢሕአዴግ በሰፊ የድምጽ ልዩነት አሸናፊ ይሆናል፡፡

ደቡብ ክልል፤

ደቡብ ክልል ውስጥ በተለይ ሀዲያና ከምባታ አካባቢ ኢሕአዴግን ሲቀናቀነው የነበረው የነ ፕ/ር በየነ ፓርቲ በከፍተኛ ደረጃ ተዳክሟል፡፡ በሚመጡት ከኹለት ዓመት ያነሱ ጊዜያት አንሰራርቶ ቢመጣ እንኳ ሊያገኝ የሚችለው ድምጽ ደኢሕዴንን የሚገዳደር አይሆንም፤ ያው በነ ፕ/ር በየነ ጠባብ ‹ቤዝ› ላይ ብቻ የተወሰነ ስለሚሆን፡፡ ሲዳማ የክልሉን ርዕሰ መስተዳድርና የደኢሕዴንን ሊቀመንበርነት ይዟል፤ ስለሆነም ከደኢሕዴን/ኢሕአዴግ ውጪ ሊመርጥ የሚችልበት ዕድል ጠባብ ነው፡፡ ወላይታና ስልጤም አሁን ባለው ሥርዓት ተጠቃሚ ነን ብለው ነው የሚያምኑት፡፡ ሌሎች ብሔረሰቦችም ቢሆኑ ከኢሕአዴግ የተሻለ አማራጭ አለ ብለው የሚስቡ አይደሉም፡፡

ደቡብ ክልል ውስጥ እነ ፕ/ር በየነ እና ሌሎች (ሊመጡ የሚችሉ) ኅብረ ብሔራዊ ድርጅቶች ድምጽ ሊያገኙ ይችላሉ ብለን ብንነሳ እንኳ፣ ሊያገኙ የሚችሉት ድምጽ የክልሉን ገዥ ፓርቲ የሚቀናቀን ይሆናል ማለት በጣም ያስቸግራል፡፡

አዲስ አበባ
***
አዲስ አበባ የአዲስ አበቤዎች ከተማ መሆኗ ከቀረ ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ ፕሮፌሰር ተገኝ ገብረ እግዚአብሔር የሚባሉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁር በቅርቡ ባቀረቡት አንድ ጥኛታዊ ጽሑፍ በግልጽ እንዳስቀመጡት በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ ውስጥ ከሚኖረው ሕዝብ መካከል 2/3ኛው ከክፍለ አገሮች (ክልሎች) የመጣ ነው፡፡ ይኽ መጠነ ሰፊ የሕዝብ ፍልሰት (ጎርፍ) የአዲስ አበባን መልክ በእጅጉ ቀይሮታል፡፡ የአዲስ አበባ ባህል፣ የአኗኗር ሥርዓት፣ አስተሳሰብ … የሚባል ነገር እየጠፋ መጥቷል፡፡ አሁን ሰዎች አዲስ አበባ ውስጥ ይኑሩ እንጂ አስተሳሰባቸውም ሆነ የአኗኗር ዘይቤያቸው የክፍለ አገር (ክልል) ነው፡፡ የሚደግፉት የፖለቲካ ድርጅት፣ የእግር ኳሽ ክለብ፣ የሚታከሙበት ሆስፒታል፣ የሚመገቡበት ምግብ ቤት ወዘተ. ብሔርን (አካባቢን) መሠረት ያደረገ ነው፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ የነበረው የኢትዮጵያዊነት ስሜት እየደበዘዘ ክልላዊነት ወይም ዘውጌ ብሔርተኝነት እየነገሠ መጥቷል፡፡

ይኽ ሁሉ የሚጠቅመው የዘውግ ድርጅቶች ግንባር የሆነውን ኢሕአዴግን ነው፡፡ ከዚህ በኋላ አዲስ አበባ ውስጥ እንደ 97 ዓመተ ምሕረቱ እና ከዚያ በፊት እንደነበረው ሁኔታ የአዲስ አበባ ነዋሪ ዘውጋዊ ማንነትን ሳያይ፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅንን ግለሰብም ሆነ ድርጅት ይደግፋል ማለት ያስቸግራል፡፡ አሁን ያለው የአዲስ አበባ ውጥንቅጡ የወጣና ገና ወጥ ማንነት (አዲስ አበቤነትን እንደገና) ያልያዘ የሕዝብ ክምችት የሚጠቅመው ኢሕአዴግን እንጂ ተቃዋሚ ድርጅቶችን አይደለም፡፡

ዐማራ ክልል
***
የዐማራ ክልሉ ገዥ ፓርቲ ብአዴን በሕዝቡ ዘንድ ያለው ተቀባይነት በጣም ደካማ ነው፡፡ ስለሆነም የዐማራ ክልል ሕዝብ በመቋቋም ላይ ያለውን አዲስ ድርጅት እና ሌሎችን ኅብረ ብሔር ድርጅች ሊደግፍ የሚችልበት ዕድል አለ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገቡት ቃል መሠረት ተቃዋሚ (ወይም በእሳቸው አነጋገር ተቀናቃኝ) ፓርቲዎች በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ ምቹ ሁኔታ የሚፈጠር ከሆነ ብአዴን ሊሸነፍ ወይም ተቃዋሚው ኀይል ባያሸንፍም ሰፊ ድምጽ (የፓርላማ መቀመጫ) ሊያገኝ የሚችልበት ዕድል አለ፡፡ ብአዴን/ኢሕአዴግ ይሸነፋል ብለን እንነሳ፡፡

የሆነ ሆኖ፣ ብአዴን/ኢሕአዴግ ቢሸነፍም እንኳ ኢሕአዴግ ኦሮሚያን፣ ደቡብን፣ ትግራይን፣ የቀሩትን የድርጅቱ ጓዶዎች (backyards) ማለትም ታዳጊ ክልሎችንና ሐረሪን እና አዲስ አበባን ይዞ ኮርቶ መንግሥት ይመሠረታል፤ ያውም በድርጅቱ ታሪክ ባልተለመደ ሁኔታ ዴሞክራሲያዊነቱ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ፡፡

ዶ/ር ዐቢይ ስለኢትዮጵያና የኢትዮጵያ አንድነት እየሰበኩ የበርካቶችን ቀልብ ስበዋል፤ በከባድ የኢሕአዴገ ተቃዋሚነቱ የሚታወቀው የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ጊዜ እንስጣቸው እያሉ ነው፤ የዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ አስተያየትም ተመሳሳይ ነው፡፡ ሰላምና መረጋጋት የሚፈልገው የንግድ ማኅበረሰቡም ከወዲሁ ዐቢይን አትቃወሙብን ማለት ጀምሯል፡፡ ከዴሞክራሲ ይልቅ ሰላም፣ መረጋጋትና የአገር ህልውና ከፍተኛ ትኩረት አግኝተዋል፡፡ ይህ ሁሉ ለጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ብቻ ሳይሆን ለኢሕአዴግም ትልቅ በረከት ነው፡፡

እኔ ከላይ ለመነሻ በጠቃቀስኳቸውና በሌሎች ነጥቦች ምክንያት መጪው ምርጫ የተበላ ዕቁብ ነው፤ ኢሕአዴግ ያሸንፋል እላለሁ፡፡ እርስዎስ?

መወያየት መልካም ነው፡፡ እስኪ እንወያይ …