Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
Maxi
Member+
Posts: 5951
Joined: 06 Mar 2014, 04:33

የትግራይ ክልል የብልፅግና ፓርቲ የካቲት 11 በዓልን ምክንያት በማድረግ ያወጣው መግለጫ!!

Post by Maxi » 18 Feb 2020, 19:37

የትግራይ ክልል የብልፅግና ፓርቲ አባላትና አመራሮች የካቲት 11 በዓልን ምክንያት በማድረግ መልዕክት አስተላለፉ :lol: :lol: :lol:

(ኤፍ.ቢ.ሲ) የትግራይ ክልል የብልፅግና ፓርቲ አባላት እና አመራሮች የካቲት 11 በዓልን ምክንያት በማድረግ መልዕክት አስተላለፉ።

የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።

አኩሪው የትግራይ ሕዝብ የጸረ ጭቆና ተጋድሎና መሰዋዕትነት በከሰሩ ሃይሎች ኣይራከስም ፤ የቡዱናዊ ፍላጎት መጠቀሚያም አይሆንም እጅግ የተከበርከውና ከባድ የህይወት መስዋእትነትን ጨምሮ ውድ ዋጋ በመክፈል እና መራራ ትግል በማካሄድ ለራስህ ብቻ ሳይሆን ለወገኖችህ የሚተርፍ ድል ያስመዘገበከው መላው የትግራይ ሕዝብ እንኳን ለ45ኛው የካቲት 11 በዓልህ በሰላም አደረስህ።

ውድ የትግራይ ህዝብ እና የተግሉ ሰማእታት ቤተሰብ እና የትግሉ ሰለባዎች በሙሉ

ከ45 ዓመታት በፊት ይደርስብህ የነበረው የዘመናት ጭቆና እና አፈና ይልቁኑም በወታደራዊው መንግስት ደርግ የተወሰዱትን መጠነ ሰፊ የግድያ፣ የአፈናና እና ጭቆና እርምጃዎችን በመቃወም በጥቂት ልጆችህ በተጀመረው ህዝባዊ መነሳሳት እና የትጥቅ ትግል በሰፊው ተቀጣጥሎ መላ ሀገሪቱ ማዳረሱ ከ29 ዓመታት በፊት ተጠናቆ ለአገራችን ኢትዮጵያ የአዲስ ጉዞ ምዕራፍ እንዲከፈት መሰረት እንዲጣል ማድረጉ የማይካድ ሐቅ ነው፡፡

ሆኖም ይህን አኩሪና የህይወት መስዋእትነትን የጠየቀው ተጋድሎ በአንድ በኩል የትግሉ ዓላማን በማጠልሸት መስዋእትነቱን ለማራከስ በሚዳክሩ የከሰሩ ሃይሎች፤ በሌላ በኩል ደግሞ የተከፈለውን ህዝባዊ መስዋእትነት ለራስ ጠባብ ቡዱናዊ ዓላማ ለማዋል በሚፈልጉ ሃይሎች መካከል በሚደረግ የገመድ ጉተታና አንቶ ፈንቶ ጨዋታ ባለቤት የሆነውን የትግራይ ህዝብ የሚጋፋ መሆኑ እንገነዘባለን።

ትግሉ እና ትግሉ የጠየቀው መስዋእትነት ተገቢውን ስፍራ ሊያገኝ ሲገባው “እሳት ተኝቶ አመድ ጐበኘው” እንዲሉ የየካቲት 11 በዓል ዝክር ተምሳሌነቱ ሕዝባዊ እምቢተኝነትና የመስዋዕትነት ተጋድሎ እሳት የተቀጣጠለበት መሆኑን ዘንግተው የትግሉን የህዝብ ልዕልና አስኳል ጥያቄ ወደ ጐን ትተው አመድ የሆነውን የፖለቲካ ጨዋታ ሊጫወቱበት ሲከጅሉ ማየት ቢያሳዝንም ታሪክ ሰሪውና አስተዋዩ የትግራይ ህዝብ በተለይም ወጣቱ ሁኔታውን በጥሞና እንደሚከታተለው በጥልቅ እንገነዘባለን፡፡

በወቅቱ በመላው ትግራይ የተቀጣጠለውን የእምቢተኝነትና የጭቆና ተጋድሎ በትጥቅና የፖለቲካ አመራርነት ጫፍ ያደረሰው መሪው ህወሓትም በብዙ ፈተናዎችና ውጣ ውረዶች አልፎ ኢትዮጵያን እስከ ቅርብ ጊዜ የመራውን ኢህአዲግ እንዲመሰረትና እንዲደራጅ ጉልህ የአመራርነት ሚናን ተጫውቷል፡፡በዚህም በመላው የትግራይ ህዝብና የትግሉን ቋያ በተቀላቀሉት ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች በአጠቃላይም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ያለው መሆኑ ላይ መተማመን ሊኖር ይገባል፡፡

የኢህአዴግ የመንግስትነት ዘመን ከነሙሉ ውስንኖቶቹ የዲሞክራሲ፣ የአንፃራዊ ሰላም እና ፍትሐዊ የሕዝቦች የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረገው ረጅም ጉዞ ጅማሬን ያረጋገጠ መሆኑን መካድ ዛሬ ከትላንት የተፈጠረ መሆኑን እንደመካድም የሚቆጠር ሲሆን፣ ዛሬን በትላንት ለመኖር የሚደረግ ሙከራም በተመሳሳይ ደረጃ የህዝብን ተጋድሎ ከንቱ የሚያደረግ መሆኑ ሊሰመርበት ይግባል።

የተሻለች የነገይቱን ኢትዮጵያ የመፍጠር ሕልማችን በታሪክ ቅብብሎሽ የሚፈፀምና ያለንባቸውን ሁኔታዎቻችን በስክነት መረዳት፣ የአሁኑ ግዜ ሁኔታዎቻችን እውነት እና አረዳድ በጋራ መግባባት ላይ መመሰረትና የወደፊት መፃኢ ጊዚያችንን በይቅር ባይነትና በመቻቻል በጊዜ ሂደት ለመቅረፅ ዘመኑ ትልቅ የአደራ ሸክም ጭኖብናል፡፡ ይህ ሸክም መላ የሀገሪቱ ሊሂቃንና ህዝቦችን የሚመለከት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።

በአሁኑ ሰዓት አገራችን ከመቸውም ጊዜ በላይ የተጋረጠባትን አጠቃላይ ውስጣዊ አደጋ ከአለማቀፋዊና አከባብያዊ ተለዋዋጭ የፖለቲካ የኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ ለውጦች ጋር አያይዞ መገምገም የችግሩ ሙሉ ስእልና መፍትሄ ለማግኘት የሚረዳ ሁኖ ሳለ አንዳንድ የፖለቲካ ሀይሎች ባረጃና ባፈጀ ክሱር የሴራ ፖለቲካ ስሌት ህዝብን ሲያደናግሩን የህዝብን መከራ ማብዛታቸው የሙሉ ጊዜ ስራ አድርገው ሲሰሩ መመልከት እጅግ አሳዛኝ ወቅታዊ ልምምድ ነው፡፡

በየካቲት 11 በተለኮሰው ህዝባዊ እንቢተኝነትና የትጥቅ ትግል የትግራይ ህዝብ መስዋእትነት የከፈለ በተሸለ የነጻነት የሰላም እና የዲሞክራሲ ጥማት ሁኖ ሳለ ከብዙ አመታት በኋላም በልዩ የፖለቲካ ውጥረትና ወከባ የትግራይ ህዝብ አሁንም የተረጋጋ አየር ለመተንፈስ አዳጋች ሁኔታ ውስጥ ይገኛል፡፡ ህዝቡ ውጥረት ውስጥ እንዲገባ ቀደም ሲል እንደተገለጸው የህዝቡን ትግል በሚያንቋሽሹ ሃይሎች እና የህዝቡን ትግል የቡዱን ትግል ለማደረግ በሚፈለጉ ሃይሎች ምክንያት እየተከሰተ ያለ መሆኑ እንገነዘባለን። ስለሆነም ጉዳዩን ለማረገብ ህዝቡ ሰላም እና ደህንነት እንዲሰማው፤ በተለያዩ ጊዜያት ከተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች ሆን ተብለው የሚሰነዘሩ ጠባጫሪ ንግግሮች በአስቸኳይ ሊታረሙ የሚገባና ለወደፊትም ጥንቃቄ ሊደረግባቸው እንደሚገባ በአፅንኦት ለማሳሳብ እወዳለሁ፡፡

ዛሬ ሃገራችንን ሰንጐ የያዛትን አክራሪ ብሄርተኛነት እና የፅንፈኝነት ክፉ በሽታ ምንጭና ምክንያት እንዳለው ልናስተውል ይገባል፡፡ የህብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝም ስርዓቱ ምስረታ የብሔር ብሔረሰቦችን ማንነት ባህልና ታሪክ ሙሉ እውቅናና ጥበቃ የሚሰጥ ሲሆን የብሔር ማንነትና የህብረብሔር አንድነት በተመጣጠነ ሚዛን ለሐገረ መንግስትነት ግንባታ ተግባር ማዋልን የሚጠይቅ፤ ይህንንም በብሔራዊ መግባባትና ቅቡልነት ባለው የህግ ስርዓት ፅኑ መሰረት ላይ የመጣል ታሪካዊ ተልዕኮ መወጣትንም ጭምር ያካትታል፡፡

ሆን ተብለው የሚወረወሩ የጥላቻ ቃላት በወቅቱ ፖለቲካ በሰከሩ የፖለቲካ፣ የሚዲያና የአክቲቪዝም ልሒቃን አቧራ ማሰባሰቢያ ዲስኩሮች ቢሆኑም አሁንና በሒደት ብዙ ዋጋ የሚያስከፍሉንና በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ላይም ጥቁር ነጥብ የሚያስቀምጡ በመሆናቸው ማናቸውም ሰብዓዊ ፍጡራንና ለሰላም ለይቅር ባይነትና ለሀቀኛ ለውጥ የሚታገሉ ሃይሎች አጥብቀው ሊኮንናቸው ይገባል፡፡

በሌላ በኩል የህዝቡን የነጻነት እና የእኩለነት ትግል ለቡደናዊ እና ግላዊ ዓላማ ለማዋል የሚደረገው ሙከራ ውጤቱ ተመሳሳይ ነው። የፖለቲካ ክስረት ዋነኛ መገለጫ ሕዝባዊ መሰረትን ማጣትና ተራማጅ የፖለቲካ ሃሳቦችን በማፍለቅ ለመምራት የሚያስችል ብቃት ንጥፈት ዋነኛ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የፖለቲካ መሪዎች የፖለቲካ ስልጣንን ከህዝብ መገልገያ መሳሪያነት ወደ ግልና ቡድናዊ የጥቅም ትስስር መጠቀሚያነት ካሸጋገሩት አመታት የተቆጠሩ ከመሆኑም ባሻገር ይህ ዝቅጠት ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ የኪሳራ ዋጋ ህዝብን እና ሀገርን እያስከፈለ ይገኛል፡፡

የፖለቲካ አመራሩን ብቃትና ንቃት በሚመለከትም ተራማጅ አስተሳሰቦችን ለመፈተሽና ፈጥኖ ለመማር ከህዝብ ተጨባጭ ፍላጐት ጋርም በማጣጣም በዝግጅት የማዳበር ስራ ባለመስራቱም የከፋ የሐሳብ ድህነትና የፖለቲካ ንቃት ጉድለት የአመራር ደረጃ ክፍተታችን ሆኖብናል፡፡

የሚዲያ ተቋማቶቻችንና ማህበረሰቡ በስፋት የሚጠቀምባቸው ማህበራዊ ሚዲያዎቻችንም የሚያወጧቸውና የሚያሰራጭዋቸው አሉታዊ መልዕክቶች ምክንያት በህዝቦቻችን መካከል ሰላምና ዴሞክራሲ እንዳያብብ አድርጎታል፡፡ በአጠቃላይ እንደ ማህበረሰብ ግንዛቤያችንና አዝማሚያችን አደገኛ አቅጣጫ መያዙን ስንገነዘብ በሚድያ መስክ ሃላፊነታችንን ለመወጣት የሰራነው ስራ ውጤት ያላስገኘ መሆኑን ለመረዳት በመስኩ የሚታየውን አጠቃላይ ምስቅልቅል መመልከት በቂ ነው፡፡

በተለይም አንዳንድ የማህበረሰብ አንቂዎች የተፅእኖ ፈጣሪነታቸውና የተቀባይነታቸው መሠረት ህዝብ እና የህዝብ ዘላቂ ፍላጐት መሆኑን በመገንዘብ ሃላፊነታቻውን በቅንነት በመወጣት በጐ ተግባር ከመፈፀም ይልቅ ሀላፊነት በጐደላቸው መልእክቶቻቸውን በመሰራጨት በህዝቦች መከከል መቃቀር በፈጠር ላይ ይገኛሉ ፡፡እነዚህ የአክቲቪዝም ሃይላት ለጊዜያዊ ጥቅምና ከንቱ ውዳሴ ሲሉ ሚዛናዊ ያልሆኑ አንዳንድ ግዜም ሃሰተኛ መረጃዎችን በመፈብረክ እና በማሰራጨት በሃገር እና ህዝብ ላይ ክህደት ሲፈፅሙ ማየት የወቅቱ አይነተኛ አደጋ ሆኖ ተጋርጦብናል፤ ይህም በመስኩ አሳዛኝ ክሽፈት ነው ብለን ልንጠቅሰው እንችላለን፡፡

ይህ ሲባል ሁሉም የሚዲያና የማበረሰብ አንቂዎች በዚህ ይፈረጃሉ ማለት ሳይሆን ለእውነትና ለህዝብ ጥቅም የቆሙ ሚድያዎችም መኖራቸው ሊዘናጋ አይገባም ፡፡

በመጨረሻም የየካቲት 11 ክብረ በዓል አከበበርና ድምቀትም በአንድ በኩል የተከፈለውን መስዋእተነትና ለማራከስ በሚፈልጉ ሃይሎች፤ በሌላ በኩል ድግሞ ህዝባዊ ትግሉን ለግልና ቡዱናዊ ፍላጎት ለማዋል በሚፈልጉ ሃይሎች ኘሮፖጋንዳ ሳይጠለሽ እንዲከበር የትግራይ ህዝብ ለዲሞክራሲ መስዋዕትነት በመክፈል የጋራ ታሪክ ያላቸው ብሔር ብሔረሰቦች በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያ እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በአጠቃላይ ማህበረሰቡ ልዩ ጥበቃ እንዲያደርጉለት ጥሪዬን እያስተላለፍኩኝ በአሉን ስናከብር ለነፃነት ለፍትህ ለሰላም ለዴሞክራሲ ሲሉ ውድ ህይወታቸውን ለከፈሉ ሰማዕታት ያለኝን የላቀ ክብር እየገለጽኩ ለመላው የትግራይ ህዝብ በአሁኑ ሰአት ወቅቱ የሚጠይቀውን የመቻቻል የአንድነት የሰላምና የብልጽግና ጉዞውን ከሌሎች ወንድማማች ህዝቦች ጋር ከማንኛውም ጊዜ በላይ ተባብሮና ተከባብሮ የሚኖርበትን እና የጋራ ብልጽግናና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥበት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡